ባለፈው እሁድ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባደረጉት ጨዋታ የተከሰተውን የዳኝነት ውዝግብ ተከትሎ በጨዋታው ዋና ዳኛ ፌዴራል አርቢቴር ኄኖክ አክሊሉ እና ረዳቱ ፌዴራል አርቢቴር ተስፋዬ ይመር ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቅጣት አስተላለፏል፡፡
በጨዋታው 48ኛ ደቂቃ የኤሌክትሪክ ተከለካይ ወደ ኃላ የመለሰውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሱሌይማና በእጁ በመያዙ የተሰጠውን 2ኛ ቅጣት ምት ፒተር ኑዋዲኬ በቀጥታ መትቶ አስቆጥሯል፡፡ ሆኖም የመሀል ዳኛው ኄኖክ ግቧን ሳያፀድቅ ቀርቶ ጨዋታው ሊቀጥል ባለበት ቅጽበት ረዳት ዳኛውን ካናገረ በኃላ ጎሏን አፅድቆታል፡፡ የኤሌክትሪክ ተጨዋቾችም ኳሱ በሌላ ተጨዋች ሳይነካ በቀጥታ መመታት አልነበረበትም በማለት ባነሱት ጥያቄ መሰረት ክስ ካስመዘገቡ በኃላ ነበር ጨዋታው የቀጠለው።
በክሱ መሰረት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጨዋታው የመሃል ዳኛ ኄኖክ አክሊሉን ለ6 ወራት ከየትኛውም ውድድሮች ሲያግድ የአርቢቴር ኄኖክን ውሳኔ ያስቀየረው ተስፋዬ ይመርን ደግሞ ከፕሪሚየር ሊግ በታች ወዳሉ ውድድሮች ዝቅ ብሎ እንደዲዳኝ ተወስኖበታል፡፡
በተያያዘ ዜና በዚሁ በ4ኛ ሳምንት አዳማ አበበ ቢቂላ ላይ አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና ባደረጉት ጨዋታ በተከሰቱ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶች ላይ የፌዴሬሽኑ ዲሲፕሊን ኮሚቴ በነገው እለት በጥፋተኛ ወገኖች ላይ ቅጣት እንደሚያስተላልፍ ታውቋል፡፡