የ2009 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከተጀመረ አንድ ወር ሊያስቆጥር ጥቂት ቀናት ቀርቶታል፡፡ በህዳር ወር መጀመርያ የተከፈተው አዲሱ የውድድር ዘመን የ4 ሳምንታት ጨዋታዎችን ያስተናገደ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም በወሩ መልካም አጀማመር ያደረጉ ተጫዋቾችን እንዲህ ቃኝታቸዋለች፡፡
ግብ ጠባቂ
ሮበርት ኦዶንካራ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለ ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ እጅግ ይቸገራል፡፡ በአለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ምክንያት የውድድር ዘመኑ መክፈቻ ያመለጠው ሮበርት ወደ ስብስቡ ከተመለሰ በኋላ በወትሮው ድንቅ ብቃቱ ቀጥሏል፡፡
ተከላካዮች
ሰኢድ ሁሴን (ፋሲል ከተማ)
አማራ ውሃ ስራን ለቆ ዘንድሮ ፋሲልን የተቀላቀለው ሰኢድ በፍጥነት ሊጉን ተላምዷል፡፡ ቡድኑ ያለፉትን 2 ጨዋታዎች በድል እንዲወጣ የመስመር ተከላካዩ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር፡፡
አንተነህ ተስፋዬ (ሲዳማ ቡና)
የሲዳማ ቡናው ተከላካይ አሁንም በወጥ አቋሙ ቀጥሏል፡፡ ከ4 ጨዋታዎች በሶስቱ ግብ ላልተቆጠረበት ሲዳማ ቡና ምርጥ ግልጋሎት ከማበርከቱ በተጨማሪ ከአበበ ጥላሁን ጋር ምርጥ ጥምረት መፍጠር ችሏል፡፡
ምንተስኖት አዳነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ዘንድሮ ባልተለመደ ቦታ ላይ ተሰልፎ ምርጥ የውድድር ዘመን ጅማሮ አድርጓል፡፡ ታታሪው ምንተስኖት ከመከላከሉ ባሻገር ለቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴም ተጨማሪ ጉልበት መሆን ችሏል፡፡ ደደቢትን በገጠሙበት ጨዋታም ግብ አስቆጥሯል፡፡
ሱሌይማን መሀመድ (አዳማ ከተማ)
አንጋፋው የአዳማ ከተማ አምበል ወሳኝ ግብ በማስቆጠር እና ለግብ በማመቻቸት ቡድኑ 6 ነጥብ እንዲያገኝ ምክንያት ሆኗል፡፡ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ተቀይሮ ቢወጣም ፣ ከ4 ጨዋታዎች በሁለቱ የማስጠንቀቂያ ካርድ ቢመለከትም ሱሌይማን በሊጉ ካሉ የግራ መስመር ተጫዋቾች በተሻለ ጥሩ አጀማመር አድርጓል፡፡
አማካዮች
ናትናኤል ዘለቀ ( ቅዱስ ጊዮርጊስ)
የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ በአራቱም ጨዋታ ተሰልፎ ምርጥ አጀማመር ማድረግ ችሏል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ የአማካይ ክፍል ላይ እርጋታን የጨመረው ናትናኤል ለቡድኑ መልካም የውድድር ዘመን ጅማሮ ከሚጠቀሱ ተጫዋቾችም ተጠቃሽ ነው፡፡
ዳዊት እስጢፋኖስ (ኢትዮ ኤሌክትሪክ)
ኢትዮ ኤሌክትሪክ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫን ባነሳ ማግስት በሊጉ ቢቸገርም ዳዊት እስጢፋኖስ በግሉ ጥሩ አጀማመር አድርጓል፡፡ ሁለት ግቦች ሲያስቆጥር በኤሌክትሪክ የአማካይ ክፍል ጠፍቶ የነበረውን ፈጠራ በመመለስ ቡድኑ ላይ ነፍስ ዘርቶበታል፡፡
ፍሬው ሰለሞን (ሀዋሳ ከተማ)
እንደ ዳዊት እስጢፋኖስ ሁሉ ከቡድኑ ደካማ አጀማመር ተነጥሎ ወጥቶ በሀዋሳ ከተማ የመጀመርያ የውድድር ዘመኑ መልከም ጅማሮ አድርጓል፡፡ የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ በፍሬው ላይ የተመሰረተ ሲሆን እንደሚፈጥራቸው የግብ እድሎች ቢሆን ሀዋሳ ከዚህ የተሻለ ውጤታማ መሆን ይችል ነበር፡፡ ፍሬው በዚህ ወር ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡
አጥቂዎች
ሽመክት ጉግሳ (ደደቢት)
የደደቢቱ የመስመር አጥቂ ቡድኑ ለሚያስቆጥራቸው ግቦች መነሻ መሆኑን ቀጥሏል፡፡ ለሶስት ግቦች መቆጠር መነሻ ከሆነው ሽመክት በተሻለ በዚህ ወር ለግቦች መገኘት አስተዋጽኦ ያደረገ የለም፡፡
ጌታነህ ከበደ (ደደቢት)
ወደ ሊጉ ከ3 የውድድር ዘመናት በኃላ ተመልሶ በግብ አዳኝነቱ ቀጥሏል፡፡ ጌታነህ በ4 ጨዋታ 5 ግቦች በማስቆጠር የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመራ ይገኛል፡፡
አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)
የደቡብ ሲቲ ካፕ ኮከብ ተጫዋቾች እና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀው የሲዳማ ቡናው አዲስ አሁንም ቡድኑ በሚፈልገው ሰአት መገኘቱን ቀጥሏል፡፡ ፈጣኑ የመስመር አጥቂ የቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ መሰረት ሲሆን በ4ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻ ላይ ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል፡፡
የህዳር ወር ኮከብ ተጫዋች ፡ ምንተስኖት አዳነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
የህዳር ወር ኮከብ አሰልጣኝ ፡ ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስ (ፋሲል ከተማ)
ሌሎች በወሩ ሞርጥ አቋም ያሳዩ ተጫዋቾች
ግብ ጠባቂዎች ፡ ወንድወሰን ገረመው (ወላይታ ድቻ) ፣ ተክለማርያም ሻንቆ (አአ ከተማ)
ተከላካዮች ፡ ፍሬዘር ካሳ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ ተክሉ ታፈሰ (ወላይታ ድቻ) ፣ ዳንኤል አባተ (አአ ከተማ) ፣ አምሳሉ ጥላሁን (ፋሲል ከተማ)
አማካዮች ፡ ዳንኤል ደምሴ (ወልድያ) ፣ ዳዊት ማሞ (አአ ከተማ) ፣ ሙሉአለም መስፍን (ሲዳማ ቡና) ፣ ክሪስቶፈር ንታምቢ (ጅማ አባ ቡና) ፣ አብዱልከሪም ንኪማ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ በዛብህ መለዮ (ወላይታ ድቻ) ፣ ዳዊት ተፈራ (ጅማ አባ ቡና)
አጥቂዎች ፡ አዳነ ግርማ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ ሐብታሙ ወልዴ (ድሬዳዋ ከተማ) ፣ ማራኪ ወርቁ (መከላከያ) ፣ ሙጂብ ቃሲም (አዳማ ከተማ)