በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ኡመድ ኡኩሪ ግብ ሲያስቆጥር ሽመልስ በቀለ ከጉዳት ተመልሷል

የግብፅ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዓርብ መደረግ ሲጀመሩ ኢትዮጵያውያን የሚገኙባቸው ፔትሮጀት እና ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ በሜዳቸው ሽንፈትን ቀምሰዋል፡፡ ፔትሮጀት በአል መስሪ እንዲሁም ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ በምስር ኤል ማቃሳ በተመሳሳይ 2-1 ተሸንፈዋል፡፡

ፔትሮጀት በሃራስ ኤል ሆዶድ ስታዲየም አል መስሪን አስተናግዶ 2-1 ተሸንፏል፡፡ ናይጄሪያዊው የቀድሞ አጥቂ ጄምስ ኦዎቦስኪኒ ፔትሮጀትን በስድስተኛው ደቂቃ መሪ ቢያደርግም በሁለተኛው አጋማሽ አህመድ ካቦሪያ እና አህመድ ጎማ ያስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች አል መስሪን ለድል አብቅተዋል፡፡ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ የነበረው ኢትዮጵያዊው አማካይ ሽመልስ በቀለ ከጉዳት መልስ በ70ኛው ደቂቃ ሃምዲ ፋቲህን ቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ ሽመልስ ከጉዳቱ ሙሉ ሙሉ ያገገመ ሲሆን የአጥቂ አማካዩ ከጉዳት መመለስ ለአሰልጣኝ ታላት የሱፍ እፎይታን ፈጥሯል፡፡

picsart_1481347404305

ኡመድ ኡኩሪ ግብ ባስቆጠረበት ጨዋታ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ በሜዳው በምስር ኤል ማቃሳ 2-1 ተሸንፏል፡፡ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ከሶስት ተከታታይ የሊግ ድሎች በኃላ ነው የተሸነፈው፡፡

ተመጣጣኝ በነበረው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ምስር ኤል ማቃሳዎች ነበሩ፡፡ ጋናዊው አጥቂ ናና ፖኩ በጥሩ ሁኔታ ተመስርቶ የመጣውን ኳስ የኤል ሃርቢ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡ ግብ ካስተናገዱ በኃላ ተጭነው ሲጫወቱ የነበሩት ኤል ሃርቢዎች በኡመድ አማካኝነት በ34ኛው ደቂቃ አቻ መሆን ችለዋል፡፡ ለግቧ መቆጠር የምስር ኤል ማቃሳው ግብ ጠባቂ ስህተት አስተዋጽኦ ነበረው፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ተጭነው መጫወት የቻሉት የፋዩም ከተማ ክለብ በናና ፓኩ ሁለተኛ ግብ አሸንፈው ወሳኝ ሶስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል፡፡ በጨዋታው ኡመድ በ63ኛው ደቂቃ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመዞበታል፡፡

ኡመድ በኤል ሃርቢ መለያ ባደረጋቸው አራት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች በጥሩ አቋም ላይ እንደሚገኝ አሳይቷል፡፡ ሁለት ግቦችን ከመረብ ሲያዋህድ አንድ ግብ የሆነ ኳስ ደግሞ አመቻችቶ አቀብሏል፡፡

ሊጉን የቀድሞ አሰልጣኙን ሆሳም ኤል ባድሪን የመለሰው አል አሃሊ በ38 ነጥብ ሲመራ ምስር ኤል ማቃሳ እና አል መስሪ በ31 እና 28 ነጥቦች ይከተላሉ፡፡ እራሱን ከሊጉ እንደሚያገል ሲናገር የነበረው ሌላኛው የካይሮ ሃያል ዛማሌክ 4 ቀሪ ጨዋታዎች እየቀሩት በ22 ነጥብ ሰባተኛ ነው፡፡

ፔትሮጀት በ24 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ በሻውኪ ጋሪብ የሚመራው ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ በ15 ነጥብ 12ተኛ ነው፡፡ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ አንድ ቀሪ ጨዋታ አለው፡፡

የኮከብ ግብ አግቢነቱን ናና ፖኩ በአስር ግቦች ይመራል፡፡ ናና ፖኩ በዘንድሮው የውድድር ዘመን እያሳየ በሚገኘው ብቃት ምክንያት ወደ ጋና ብሄራዊ ቡድን እንዲጠራ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የ15ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በቀጣይ ማክሰኞ አሌክሳንደሪያ ከተማ ላይ በቦርጅ ኤል አረብ ስታዲየም ሰሞሃ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢን ሲያስተናግድ ረቡዕ በፔትሮስፖርት ስታዲየም ዛማሌክ ፔትሮጀትን ይገጥማል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *