በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት ሲመለስ ኢትዮጵያ ቡና ደረጃውን አሻሻለ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተስተካካይ ጨዋታዎች መድመቁን ቀጥሏል፡፡

ቅዳሜ እና እሁድ በተደረጉ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ጨዋታዎችም ሲዳማ ቡና ከፍተኛ የደረጃ መሻሻል ያሳየበትን ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ የነጥብ ልዩነቱን ያሰፋበትን እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የገባበትን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

ቅዳሜ በ9 ሰአት ይርጋለም ላይ ደደቢትን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና በአጥቂው ብሩክ አየለ ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፏል፡፡ የመጀመርያውን ዙር ጨዋታዎች ያጠናቀቀው ሲዳማ ቡና ከድሉ በኋላ ከነበረበት 10ኛ ደረጃ ወደ 6ኛ ደረጃ ሲያድግ 3 ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ደደቢት በበኩሉ አንድ ደረጃ ዝቅ ለማለት ተገዷል፡፡

በ11፡30 ሀዋሳ ከነማን ያስተናገደው ኢዮጵያ ቡና ከሀዋሳ ጠንካራ ፈተና ገጥሞት 3-2 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወጥቷል፡፡ ለአደገኞቹ በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኘው ኤፍሬም አሻሞ በ22ኛው ፣ ፋሲካ አስፋው በ42ኛው እና ዴቪድ በሻ በ77ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥሩ ለእንግዳው ቡድን ሀዋሳ ከነማ ጋዲሳ መብራቱ በ36ኛው ፣ ግሩም አሰፋ በ48ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል፡፡ ሀዋሳ ከነማ 2ጊዜ ተመርቶ አቻ የሚሆንበትን እድል ሲያገኝ በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ በርካታ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን እንደመፍጠራቸው መሸነፋቸው አስቆጭ ሆኗል፡፡

ከጨዋታው መጀመር በፊት ኢትዮጵያ ቡናን ለ8 አመታት ያገለገለው እና በደጋፊዎቹ እጅግ የሚወደደው ታፈሰ ተስፋዬ በስጦታ የታጀበ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

እሁድ በተደረገው የንግድ ባንክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳሙኤል ሳኑሚ በ49ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸንፎ ከተከታዩ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 8 አስፍቷል፡፡ ጨዋታው ውጥረት የበዛበት እና ብዙም ክፍተት ያልነበረበት ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች የንግድ ባንክን የተከላካይ መስመር መጣስ ተስኗቸው የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ከርቀት በሚሞከሩ ኳሶች ብቻ ለመፍጠር ተገደዋል፡፡ በ3-5-2 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት ንግድ ባንኮች በአማካይ ክፍሉ ላይ የበላይነት ቢኖራቸውም በርካታ የግብ እድል መፍጠር ተስኗቸው አምሽተዋል፡፡

ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እያለው በ33 ነጥብ ሲመራ በተመሳሳይ አንድ ጨዋታ የሚቀረው ኢትዮጵያ ቡና በ25 ነጥብ ይከተላል፡፡ የግብ አግቢነቱን ሰንጠረዥ ኡመድ ኡኩሪ በ9 ግቦች ይመራል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ