በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ – ኢትዮጵያ ቡና ከመሪው ያለውን ርቀት አጠበበ

በ11 ሰአት የተደረገው የሁለቱ ሃያላን ፍልሚያ በብዙዎች እንደመጠበቁ ስታዲየሙ በአመዛኙ በተመልካች ተሞልቷል፡፡ ደደቢት መብራት ኃይልን ፤ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ መከላከያን አሸንፈው በጥሩ መነቃቃት ጨዋውን እንደማድረጋቸው ከፍተኛ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ቢጠበቅም ያን ያህል የተመልካችን ቀልስ ሳይገዛ በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በመጀመርያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና የተሸለ ሆኖ ሲቀርብ በአስቻለው ግርማ እና ኤፍሬም አሻሞ አማካኝነት ጥቃት ለመፈፀም ሙከራ አድርገዋል፡፡ በተለይም በቀኝ መስመር በኩል አስቻለው ግርማ ብርሃኑ ቦጋን በእጅጉ ሲፈትነው አምሽቷል፡፡በ5ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ ከቅጣት ምት ያሻገራት እና ከግብ አፋፍ እንደምንም የተመለሰችው ኳስ በመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀስ የግብ ማግባት አጋጣሚ ነበር፡፡

የመጀመርያው አጋማሽ የኃይል አጨዋወት የበዛበት እና ማራኪ ያልበረ ሲሆን ሁለቱም ወደ መስመር አዘንብለው ለማጥቃት ያደረጉት ጥረት ፍሬ ማፍራት አልቻለም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያው የተሸለ እና በግቦች የታጀበ እንቅስቃሴ ታይቷል፡፡ በ49ኛው ደቂቃ ኤፍሬም አሻሞ ኢትዮጵያ ቡናን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ከመረብ ሲያሳርፍ ብዙም ሳይቆይ በ51ኛው ደቂቃ ኤፍሬም አሻሞ ወደ ግብ ያጠፋትን ኳስ ተከላካዩ ዘነበ ከበደ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ ኢትዮጵያ ቡና 2-0 እንዲመራ አስችሎታል፡፡

በ5 ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ግብ የተቆጠረባቸው ደደቢቶች አፀፋ ለመመለስ ያደረጉት ጥረት በቶክ ጀምስ በሚመራው የተከላካይ ክፍል ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡ ደደቢት በ85ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በገባው ሄኖክ ኢሳያስ ግብ ወደ ጨዋታው ቢመለስም ከቆሙ ኳሶች በስተቀር ይህ ነው የሚባል የግብ ማግባት መፍጠር ተስኗቸው ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ኢትዮጵያ ከጣፋጭ ድል በኋላ ነጥቡን ወደ 22 ከፍ ሲያደርግ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነትም ወደ 8 አጥብቧል፡፡ ደደቢት በበኩሉ በ15 ነጥቦች ባለበት 6ኛ ደረጃ ለመርጋት ተገዷል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ