ቻምፒዮንስ ሊግ ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አልጄርያ ተጉዟል

በ2015 የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን የሚወክለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ትላንት ሌሊት ወደ አልጄርያ ተጉዟል፡፡ 18 ተጫዋቾችን ጨምሮ 26 የልኡካን ቡድን ይዞ የተጓዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በግብፅ አድርጎ አልጄርያ ዋና ከተማ አልጀርስ የተጓዘ ሲሆን ከአልጀርስ 200 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደሚገኘው የተጋጣሚው ኤም ሲ ኡልማ ስታድየም ክለቡ ባዘጋጀላቸው አውሮፕላን እንደሚጓዙ ታውቋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ 18ቱም ተጫዋቾቹ በሙሉ ጤንነት ላይ የሚገኙለት ሲሆን በቅርቡ የፈረሙት አጥቂዎቹ ዩጋንዳዊው ብሬይን ኡሞኒ እና ብራዚላዊው ኤልተን ሳንቶስ ከቡድኑ ጋር አብረው ተጉዘዋል፡፡ ቡድኑን በድጋሚ መቀላቀሉ የተነገረው ኡመድ ኡኩሪ ግን ኢንተርናሽናል የዝውውር ሰርቲፍኬት ባለማግኘቱ ከቡድኑ ጋር እንዳልተጓዘ ተነግሯል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአልጄርያ ሊግ 10ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ኤምሲ ኡልማ የሚያደርገው ጨዋታ ቅዳሜ ምሽት 12፡00 የሚጀምር ሲሆን የቱኒዚያ ዳኞች እና ማሊያዊው ኮሚሽነር ጨዋታውን ይመሩታል፡፡

 

ያጋሩ