​የጨዋታ ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ ያለግብ አቻ ተለያይተዋል

አምስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ቀጥሎ ሲውል በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ያለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በጨዋታው ሁለቱ ቡድኖች በአጠቃላይ የግብ ሙከራዎች እና በጨዋታ ቁጥጥር ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን ከርቀት ወደግብ ከሚደረጉ ሙከራዎች ውጪ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ግን በጨዋታው ለመመልከት አልተቻለም ነበር።

በጨዋታው መጀመሪያ ወደግብ በመቅረብ የተሻሉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በ5ኛው ደቂቃ በሳላህዲን ሰዒድ አማካኝነት ማድረግ ችለዋል። በ15ተኛው ደቂቃ ምኞት ደበበ ሳልሃዲን ሰዒድ ላይ በሰራው ጥፋት ምክኒያት የተገኘውን ቅጣት ምት አበባው ቡጣቆ በቀጥታ ሞክሮ ለጥቂት ከግቡ አናት ወደላይ ወጥቶበታል።

በ20ኛው ደቂቃ ታፈሰ ተስፋዬ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ያገኘውን ኳስ ወደግብ አክርሮ ቢመታም የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ አውጥቶበታል። ከርቀት በሚመቱ ኳሶች ሮበርትን መፈተን የጀመሩት አዳማዎች በዳዋ ሁጤሳ አማካኝነት በ28ኛው እና በ42ኛው ደቂቃ ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ቅዱስ ጊዮርጊሶችም በተመሳሳይ ግብ በማስቆጠር መሪ ለመሆን ጥረት ያደረጉ ሲሆን በሃይሉ አሠፋ እና ሳልሃዲን ሰዒድ ከሳጥኑ ውጪ የመቷቸው ኳሶች ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።

በ37ኛው ደቂቃ ተስፋዬ በቀለ በተከላካይ መስመር ላይ ያመለጠውን ኳስ ለማውጣት በሚሞክርበት ጊዜ ምንተስኖት አዳነ ላይ ጥፋት ሰርቷል በሚል ፍፁም ቅጣት ምት እንዲሰጣቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ቢያመለክቱም የጨዋታው ዳኛ ግን በዝምታ አልፈዋል። ዘንድሮ ከተከላካይ ስፍራ እየተነሳ የአጥቂ መስመሩን በማገዝ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ምንተስኖት አዳነ በመጀመሪያው አጋማሽ የባከኑ ደቂቃዎች ላይ ግብ ማስቆጠር ችሎ የነበረ ቢሆንም ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ ስለነበር ግቡ ሳይፀድቅ ቀርቷል።

picsart_1481483372099

ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ከመጀመሩ በፊት ሁለቱም ክለቦች የአጨዋወት መንገዳቸውን ለመቀየር የተጫዋች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በአዳማ በኩል አዲስ ህንፃ እና ሲሳይ ቶሊ፤ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ናትናኤል ዘለቀ ተቀይረው ገብተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ በአብዛኛው ከረጅም ርቀት የሚመቱ ዒላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ውጪ የሚጠቀስ የግብ አጋጣሚ አልተፈጠረም። የጨዋታው መደበኛ ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ በባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ አዳማ ከተማ ያገኘውን ቅጣት ምት ሱሌይማን መሐመድ መትቶ ሮበርት በአስገራሚ ሁኔታ ያወጣበት ኳስ ለክለቡ የምታስቆጭ ነበረች።

ጨዋታውን የመሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ከአዳማ ከተማ በኩል 6፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ለ2 ተጫዋቾች የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ አሳይተዋል። በጨዋታው መገባደጃ ናትናኤል ዘለቀ የተከላካይ መስመሩን አምልጦ ወደግብ እየሄደ በነበረው ታፈሰ ተስፋዬ ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠው ቢጫ ካርድ ቀይ መሆን ነበረበት በሚል ከአንዳንድ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ተቃውሞ ገጥሞታል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ5 ጨዋታዎች በሰበሰበው 10 ነጥብ የሊጉ ሰንጠረዥ አናት ላይ ተቀምጦ የሚቀጥል ሲሆን በተመሳሳይ ጨዋታ 8 ነጥቦች ያሉት አዳማ ከተማ ደግሞ ሲዳማ ቡና እና ደደቢትን ተከትሎ በ4ተኛነት ተቀምጧል።

ፕሪምየር ሊጉ በቀጣዩ ሳምንት ቅዳሜ እና እሁድ በ6ተኛ ሳምንት ጨዋታዎች የሚቀጥል ይሆናል። በሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ይርጋለም ተጉዞ በሁለተኛነት የሚከተለውን ሲዳማ ቡና ሲገጥም አዳማ ከተማ በበኩሉ ወልዲያን ያስተናግዳል።

የአሠልጣኞች አስተያየት

picsart_1481483289880

አሸናፊ በቀለ – አዳማ ከተማ

“ጊዮርጊስ አገራችን ውስጥ አሉ ከሚባሉ ትልቅ ቡድኖች አንዱ እና ለብዙ ጊዜ ሻምፒዮን የሆነ ቡድን ነው። በበርካታ ደጋፊዎቹም ታጅቦ ይጫወታል፤ ብዙ ተጫዋቾችንም ለብሔራዊ ቡድን ማስመረጥ ችሏል። ይህን ቡድን ብናሸንፍ ደስ ይለን ነበር፤ ግን አቻ ውጤቱ ለኛ መልካም ነው።”

“ውድድሩ በታክቲካል ዲሲፕሊን የታጠረ ነው፤ የአሠልጣኞች ጨዋታ ነበር ማለት ይቻላል።”

“ሁለቱም ቡድኖች ካላቸው የማሸነፍ ፍላጎት የተነሳ ሃይል የተቀላቀለበት ጨዋታንም ተመልክተናል። ዳኛው ይህንን መቆጣጠር በመቻሉ ግን ሳላደንቀው አላልፍም።”

“በመጀመሪያው አጋማሽ ጊዮርጊስ የግብ አጋጣሚዎችን በመፍጠር የተሻለ ነበር። ይህንን መግታት ነበረብን። ስለዚህ በመጀመሪያው አጋማሽ አጥቂ የነበረውን ሙጂብ ቃሲም የተከላካይ ክፍሉን ለማጠናከር ወደኋላ መልሼው ነበር። ተጫዋቾቼ ሁለገብ መሆናቸው ይህን እንድናደርግ አስችሎናል።”

picsart_1481483250493

ማርት ኖይ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

“ጨዋታው ጥሩ ነበር። ስታዲየሙ ሙሉ ነበር፤ ሁለቱም ቡድኖችም የቻሉትን ያህል ለመጫወት ሞክረዋል።”

“ከአዳማ ከተማ ጋር ባደረግናቸው የመጨረሻዎቹ 4 እና 5 ጨዋታዎች ላይ ፈትነውናል። ጥሩ የተከላካይ ክፍል ስላላቸው ዛሬም ግብ ለማስቆጠር ተቸግረን ታይተናል።”

“የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቀላል ውድድር አይደለም። በተለይ ከአዲስ አበባ ውጪ የምናደርጋቸው ጨዋታዎች ሁሌም አስቸጋሪ ናቸው። ባለፈው ሳምንት ጎንደር ላይ ከፋሲል ጋር ባደረግነው ጨዋታ ተሸንፈናል፤ ዛሬ ደግሞ በሊጉ ካሉ ጠንካራ ክለቦች ከአንዱ ጋር አቻ ተለያይተናል። እነዚህ ጨዋታዎች የውድድሩ ትንሽ ክፍል ናቸው፤ እሱን ረስተን ቀጣዩ ጨዋታ ላይ ነው ማተኮር ያለብን።”

Leave a Reply