​የጨዋታ ሪፓርት| ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ድል አስመዝግቧል 

ሁለቱን የአዲስ አበባ ክለቦች ባገናኘው የ5ኛው ሳምንት ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመመራት ተነስቶ አዲስ አበባ ከተማን 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የውድድር አመቱን የመጀመሪያ ድል አስመዝግቧል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ተቆጣጥረው በመጫወት ለማጥቃት እና ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ ግብ ለማስቆጠርግ ሲጥሩ ተስተውሏል፡፡

በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የግብ ክልል በመድረስ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ ከነዚህም መካከል በጨዋታው ለወትሮው ከሚታወቅበት የተከላካይ አማካይነት ሚና በተለየ በዛሬው ጨዋታ ቡድኑ በተከተለው በ4-1-4-1 የአጨዋወት ዘዴ አጥቂ ጀርባ ካሉት አማካዮች አንዱ ሆኖ የተጫወተው አምበሉ ታዲዮስ ወልዴ በ3ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር አንተነህ ያሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ የሞከረውና የግቡ ቋሚ የመለሰበት የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በ2ኛው ደቂቃ ታዲዮስ በተመሳሳይ ያገኘውን ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማዎች በ8ኛው ደቂቃ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ያገኟትን ኳስ ፍቃዱ አየለ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ፌቮ ካዳነበት ውጪ በመጀመሪያው 15 ደቂቃ ብልጫ ተወስዶባቸው ነበር፡፡

ከወትሮው በተሻለ ማጥቃትን መርጠው ወደ ሜዳ የገቡ የሚመስሉት ንግድ ባንኮች በ23ኛው ደቂቃ ቢኒያም በላይ እና ፍቅረየሱስ በማራኪ ሆኔታ ተቀባብለው ከገቡ በኃላ ፍቅረየሱስ ለአዲሱ ሰይፉ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አዲሱ ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ ሌላኛው በኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ ከተገኙ የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች የሚጠቀስ ነበር፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በመጀመሪያው አጋማሽ ካሳዩት የመጫወት እና የማሸነፍ ፍላጎት ተቀዛቅዘው የታዩ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ኳስን መስርቶ ከመጫወት ይልቅ ከተከላካይ በሚለጉ ረጃጅም ኳሷች ለመጠቀም ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡

በ49ኛው ደቂቃ ዮናታን ብርሃነ ለፍቃዱ አየለ የመቻቸውን ያለቀለት ኳስ ፍቃዱ በመዘግየቱ ኢማኑኤል ፌቮ ቀድሞ ኳሷን ያዘበት እንጂ ግብ ለመሆን የቀረበ አጋጣሚ ነበር፡፡

በ77ኛው ደቂቃ አማረ በቀለ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ የንግድ ባንኩ ተከላካይ አንተነህ ገብረክርስቶስ ሲመልስ ግብ ክልሉ ጠርዝ ላይ የነበረው ዘሪሁን ብርሃኑ ኳሷ እንደመጣች በግሩም ሁኔታ አክርሮ ከመረብ በማዋሃድ አዲስ አበባ ከተማን ቀዳሚ አድርጓል፡፡

picsart_1481485259213

የአዲስአበባ ከተማ መሪነት ሊዘልቅ የቻለው ለ3 ያክል ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡ በ80ኛው ደቂቃ አንተነህ ገብረክርስቶስ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ የአዲስ አበባ ከተማው ግብጠባቂ ተክለማርያም ለማራቅ ሞክሮ ከፒተር ጋር በመጋጨቱ ያለፈችውን ኳስ ለማውጣት ሶስት የአዲስ አበባ ተከላካዮች ጥረት ሲያደርጉ ፍቅረየሱስ ላይ ጥፋት በመስራታቸው የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ግዙፉ ናይጂሪያዊ አጥቂ ፒተር ኑዋድኬ ከመረብ አዋህዶ ቡድኑን አቻ አድርጓል፡፡

picsart_1481485333704

ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል ተብሎ ሲጠበቅ በ82ኛው ደቂቃ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃንን ተክቶ የገባው ሳሙኤል ዮሀንስ በ90ኛው ደቂቃ ከቢንያም ሲራጅ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ በአዲስ አበባ ተከላካዮች የትኩረት ማነስ ታግዞ የቡድኑን ወሳኝ የማሸነፍያ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የ2009 የውድድር ዘመን የመጀመርያ 3 ነጥቡን ማሳካት ችሏል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

picsart_1481485360145

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ – አአ ከተማ

“በመጀመሪያው አጋማሽ ባንኮች ከኛ የተሻሉ ነበሩ፡፡ በ2ኛው አጋማሽ ደግሞ ቡድናችን እንደ ቡድን የተሻለ ስለነበር ቀድመን ግብ ልናስቆጥር ችለናል፡፡ ነገር ግን እኛ ላይ የተቆጠረው የመጀመሪያ ጎል አግባብ አልነበረም፡፡ በህጉ መሰረት 16፡50 ውስጥ ግብ ጠባቂው ጥበቃ ሊያገኝ ይገባል፡፡ ሆኖም የዳኛን ውሳኔ ከነስህተቱ መቀበል ግድ ይለናል፡፡”

” ጥቃቅን የዳኝነት ስህተቶች የጨዋታን ውጤት ሊቀይሩ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል፡፡”

“በተደጋጋሚ እንደተናገርኩት የቡድናችን ዋነኛ ችግር አጨራረስ ላይ ነው፡፡ በዛሬው ጨዋታ ላይ እንኳን በርካታ የግብ እድሎችን አምክነናል፡፡ ነገር ግን በሂደት ይህን ችግር ለመቅረፍ ጥረት እናደርጋለን፡፡”

picsart_1481485286771

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

“በዘንድሮ የውድድር ዘመን ካደርግናቸው ሶስት ጨዋታዎች በተሻለ መልኩ ዛሬ ተንቀሳቅሰናል፡፡ ቡድናችን በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በቅንጅት የተሻለ ነበር ፤ ይህም ቡድናችን ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ መምጣቱን ያሳያል፡፡ ስለዚህ የዛሬው ድል በቀጣይ ለቡድናችን የራስ መተማመን የሚጨምር ይሆናል፡፡”

” ከከፍተኛ ሊግ ካደጉት ጅማ እና ወልዲያ ጋር ከሜዳችን ውጪ ያደረግናቸው ጨዋታዎች አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ ሁለቱም ቡድኖች በሜዳቸው በጠንካራ ድጋፍ ታግዘው ፈትነውናል፡፡ በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ ያጣናቸው ነጥቦች አይቆጩንም፡፡ ነገርግን በሜዳችን ማግኘት ከሚገባን 6 ነጥቦች 4 ማግኘታችን ካለን የቡድን ጥበት አንፃር ጥሩ የሚባል ነው፡፡”

Leave a Reply