ፊሊፕ ዳውዚ በመጨረሻ ሰአት ክለቡን ታደገው

የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረጉ 2 ከባድ ግምት በተሰጣቸው ተስተካካይ ጨዋታዎች ደምቆ አምሽቷል፡፡

በ9፡00 የተደረገው የመከላከያ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፍልምያ በአዝናኝ እንቅስቃሴዎች ፣ በግብ ሙከራዎች ፣ በመጨረሻ ሰአት ግቦች እና በአስደናቂ ግቦች ታጅቦ 3-3 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ መከላከያዎች በኳስ ቁጥጥር እና በተደጋጋሚ ወደ ግብ በመድረስ ከንግድ ባንክ የተሸለ ሆኖ ቢታዩም የመጀመርያ ግባቸውን ለማግኘት እስከ 28ኛው ደቂቃ ድረስ ጠብቀዋል፡፡ በንግድ ባንክ የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሲሳይ ደምሴ በአግባቡ ተጠቅሞበት መከላከያን መሪ አድርጎታል፡፡ በእለቱ በመሃል ተከላካይነት የተጫወተው ሲሳይ በውድድር ዘመኑ 3ኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግቡ ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ንግድ ባንክ ይህ ነው የሚባል ጫና መፍጠር ባይችልም በ44ኛው ደቂቃ የግራ መስመር ተከላካዩ መሃሪ መና በግራ የፍፁም ቅጣት ምት ጠርዝ ላይ ያገኛትን ኳስ አክርሮ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ በአቻ ውጤት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያ ይበልጥ ተሻሽሎ ቀርቧል፡፡ በፈጣን ቅብብል ወደ ግብ መድረስ ሲችሉ ኳስ ከእግራቸው ስትወጣ መልሰው ለመቀበል ያላቸው ተነሳሽነት ግሩም ነበር፡፡ የመከላከያ ጫና ፍሬ ማስገኘት የጀመረው ገና በ47ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ታዬ ግብ 2-1 መምራት ሲጀምሩ ነበር፡፡ ከግቧ መቆጠር በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት መከላከያዎች ፍሬው ሰለሞን በ64ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ መሪነታቸውን ወደ 3-1 አስፍተዋል፡፡

በጨዋታው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እጅግ ተዳክሞ እንደመቅረቡ እስከ 89ኛው ደቂቃ ድረስ የነበረው የመከላከያ የ3-1 መሪነት ጨዋታውን ያበቃለት አስመስሎት ነበር፡፡ ሁሉም ነገር የተቀየረው በ89ኛው ደቂቃ በመከላከያ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ፊሊፕ ዳውዚ ተጠልፎ ከተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት በኋላ ነው፡፡ ናይጄርያዊው አጥቂ የፍፁም ቅጣት ምቱን ወደግብ ቀይሮ ቡድኑን ነፍስ ሲዘራበት ከ2ደቂቃዎች በኋላ በጭማሪ ሰአት ግብ ጠባቂው ይድነቃቸውን ጭምር አልፎ ለንግድ ባንክ አቻ የምታደርገውን ግብ አስቆጥሯል፡፡

ካልተጠበቀው የአቻ ውጤት በኋላ ንግድ ባንክ በ23ነ ነጥብ 2ኛ ደረጃነቱን ሲያስጠብቅ መከላከያ በ18 ነጥብ 5ኛ ደረጃን ይዟል፡፡

{jcomments on}

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *