ኡመድ ኡኩሪ ግብ ማስቆጠሩን ቀጥሏል

ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ኡመድ ኡኩሪ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት ክለቡ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ከሰሞሃ ጋር 1-1 በተለያየበት ጨዋታ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ሽመልስ በቀለ የሚጫወትበት ፔትሮጀት ደግሞ በሃያሉ ዛማሌክ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ተሸንፏል፡፡

በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ የሚገኘውን ሰሞሃን ከሜዳው ውጪ አሌክሳንደሪያ ላይ የገጠመው ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ 1 አቻ በሆነ ውጤት ጨዋታውን ጨርሷል፡፡ ኤል ሃርቢ በ87ኛው ደቂቃ በኡመድ ግብ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ከሁለት ደቂቃዎች ቆይታ በኃላ ባኑ ዲያዋራ ባለሜዳዎቹን አቻ አድርጓል፡፡ ኡመድ በውድድር ዘመኑ ጥሩ አቋም ላይ የሚገኝ ሲሆን በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ያስቆጠራቸውን የግብ መጠኖች ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል፡፡

በፔትሮስፖርት ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ዛማሌክ ፔትሮጀትን 1-0 በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል፡፡ ሽመልስ በቀለ በጨዋታው ላይ ለ77 ደቂቃዎች መጫወት የቻለ ሲሆን በ77ኛው ደቂቃ በናይጄሪያዊው ቪክቶር ዲያቢ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ የካይሮውን ሃያል ለድል ያበቃች ግብ በ61ኛው ደቂቃ የፔትሮጀቱ ግብ ጠባቂ ካሪም ታሪክ በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሯል፡፡

ሊጉን በኤንፒ ነጥብ የጣለው አል አሃሊ በ39 ነጥብ ሲመራ ምስር ኤል ማቃሳ እ ኤል መስሪ በ34 እና 31 ነጥብ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ናቸው፡፡ ሽንፈቱን ተከትሎ ፔትሮጀት በ24 ነጥብ ስድስተኛ ሲሆን አንድ ቀሪ ጨዋታ የሚቀረው ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ በ16 ነጥብ 12 ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply