ኢትዮጵያዊው የኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ የፊት መስመር ተሰላፊ ኡመድ ኡኩሪ በወሩ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ለክለቡ ምርጥ ብቃቱን ማሳየት ችሏል፡፡ ክለቡ ካደረጋቸው ስድስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ውስጥ ኡመድ ሶስት ግቦች ሲያስቆጥር አንድ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡
ኡመድ በሂደት ከቡድኑ ጋር መዋሃድ የቻለ ሲሆን አሁን ላለበት ብቃት መድረስ ሚስጥር ያለውን ከካይሮ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ተናግሯል፡፡ “የተለየ ሚስጥር የለውም፡፡ ዋናው በራስ-መተማመን መቻል ነው፡፡ በቀድሞ ክለቤ (ኤንፒ) ለአንድ ዓመት የሚያክል ግዜ አልተጫወትኩም ነበር፡፡ መጫወት አለመቻል ደግሞ በአዕምሮ ላይ ጫናን ይፈጥራል፡፡ ሁለተኛ እድል አግኝተህ ስትሰራ ደግሞ በራስ መተማመንህን ዳግም ታገኘዋለህ፡፡ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ መግባቴ በራስ-መተማመኔን ጨምሮታል፡፡ መጫወት ባለመቻልህ ኳስ አይጠፋብህም ፤ ግን በራስ-መተማመንህ ይወርዳል፡፡ እኔም ደግሞ የአካል ብቃቴን በግሌ መጠበቅ በመቻሌ ወደ ጨዋታ ስመለስ ነገሮች አላስቸገሩኝም ነበር፡፡ ፊትነስ ባይሮርህ ለጨዋታ ትቸገር ነበር፡፡” ይላል ኡመድ፡፡
ኡመድ ሲቀጥል በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲጫወት ከሚሰጠው ሚና በተለየ ከመስመር እየተነሳ መጫወቱን እምብዛም እንዳልከበደው ይናገራል፡፡ “ብዙ ጊዜ ከመስመር እየተነሳው እንድጫወት ነው የሚያደርጉኝ፡፡ ኢትሃድ አሌክሳንደሪያ እያለው ሆሳም ሃሰን (ታዋቂው የቀድሞ የግብፅ አጥቂ አሁን የአል መስሪ አሰልጣኝ ነው) ከመስመር እንድነሳ ነበር የሚያደርገኝ፡፡ ቦታው ስለለመድኩት ለመጫወት አልቸገረኝም፡፡”
የኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢው አሰልጣኝ ሻውኪ ጋሪብ ከተጫዋቾቻቸው ጋር መልካም የሆነ የስራ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል፡፡ አሰልጣኙ ለረጅም ዓመታት ፈርኦኖቹን በምክትል እና ዋና አሰልጣኝነት ያሰለጠኑ ሲሆን አሁን ደግሞ ከኡመድ ጋር የመስራት እድልን አግኝተዋል፡፡ “ከሻውኪ ጋሪብ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡ በእኔ ዕምነት አለው፡፡ ሁሌም ነፃ ሚና ነው ሜዳ ውስጥ የሚሰጠኝ፡፡ እንደፈለግህ ተጫወት ነው የሚለኝ፡፡” ይላል ኡመድ ስለግብፃዊው አሰልጣኙ፡፡
ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ የሊግ ውድድሩ ዘመን ሲጀመር በመልካም ሁኔታ ላይ አይገኝም ነበር፡፡ የግብፅ አየር ሃይል ክለብ የሆነው ኤል ሃርቢ 18 ክለቦች ከሚወዳደሩበት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ያስገደደው በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ያጣው ነጥቦች ናቸው፡፡ “የውድድር ዘመኑ ሲጀመር የምንከተለው ታክቲክ ልክ አልነበረም፡፡ አሰልጣኛችን አምስት ተከላካዮችን ነበር የሚጠቀመው፡፡ ሶስቱ የመሃል ተከላካዮች በመሆናቸው መሃል ሜዳ ላይ አንድ ትርፍ ሰው ይቀር ነበር፡፡ አይተህ ከሆነ አናጠቃም ነበር፡፡ በአብዛኛው ስንከላከል ነበር፡፡ እኔ ግብ ባስቆጠርኩበት ጨዋታ ኤል ጋይሽን 3-0 ካሸነፍን በኃላ የምንጠቀመውን ታክቲክ ለወጥነው፡፡ 4-5-1 እንዲሁም 4-3-3 መጠቀም ጀመርን፡፡ ከዛ በኃላ በውጤትም፣ በአጨዋወትም የተሻለ ውጤታማ መሆን ችለናል፡፡”
ኡመድ ከአሁን በሌሎች ክለቦች ዕይታ ውስጥ መግባት እየቻለ ነው፡፡ “አዎ እኔን የሚፈልጉ ክለቦች አሉ፡፡ ወኪሌ (አቡዱልራህማን መግዲ) ነው በብዛት የሚያውቀው፡፡ እኔ ትንሽ አንዳልዘናጋ ወኪሌ እምብዛም ስለዚህ ጉዳዮች አይነግረኝም፡፡ ከሶስት ወይም አራት ሳምንታት በፊት ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ውሌን የማደስ ፍላጎት እንዳላቸው ወኪሌ ነግሮኝ ነበር፡፡ እኔ ግን አሁን ላይ ስለውል ማራዘም የማሰብበት ይሁን የማወራበት ግዜ ላይ አይደለሁም፡፡ ጊዜው ስላልሆነ ወኪሌን አሳውቂያለው፡፡ አሁን የማስበው ኳስ ስለመጫወት ብቻ ነው፡፡” ሲል ሃሳቡን አጠናቅቋል፡፡
የግብፅ ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዙር ሊጠናቀቅ ሶስት ጨዋታዎች የቀሩ ሲሆን ፈርኦኖቹ ለአፍሪካ ዋንጫው ዝግጅት እንዲሁም በጋቦን 2017 ተሳታፊ ስለሚሆኑ ሊጉ ለአንድ ወር ያክል ይቋረጣል፡፡ በዚህም የተነሳ አንደኛውን ዙር በቶሎ ለማጠናቀቅ ክለቦች በሶስት እና አራት ቀናት ልዩነት ጨዋታ እንዲያደርጉ ተገደዋል፡፡