የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በ4ኛው ሳምንት . . . .

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ መደረግ ጀምረው ሀሙስ በተደረገ ጨዋታ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ ደደቢት ፣ አዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ በአሸናፊነታቸው ሲቀጥሉ መከላከያ እና ንግድ ባንክ የአመቱ የመጀመርያ ነጥባቸውን ጥለዋል፡፡

 

ምድብ ሀ

ባህርዳር ላይ ጥረት ኮርፖሬት አዳማ ከተማን አስተናግዶ 2-1 የተረታበት ጨዋታ የ4ኛው ሳምንት መክፈቻ ነበር፡፡ ድሉን ተከትሎ አዳማ ያደረጋቸውን 4 ጨዋታዎች በሙሉ በማሸነፍ በ12 ነጥብ ከደደቢት እኩል ከአናት እንዲቀመጥ ሲያስችለው የፈረሰው ዳሽን ቢራን የተረከበው ጥረት ተከታታይ ሁለት የሜዳው ጨዋታዎችን ተሸንፎ ወደ ሰንጠረዡ ወገብ ተንሸራቷል፡፡ ሰኞ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማን 2-0 ሲያሸንፍ ደደቢት ቦሌ ክ/ከተማን በቀላሉ 6-1 አሸንፏል፡፡  የአምናው ቻምፒዮን ደደቢት ዘንድሮም ክብሩን ለማስጠበቅ በሚችልበት አቋም ላይ ያለ ይመስላል፡፡ ያደረጋቸውን 4 ጨዋታዎች በሙሉ በማሸነፍ በ15 የግብ ልዩነት የምድቡ ቁንጮ ሆኗል፡፡

picsart_1481865003436

ማክሰኞ በተደረጉ ጨዋታዎች 5:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ድሬዳዋ ከተማን የገጠመው ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ 2-0 የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ድል አሳክቷል፡፡ 3 ተከታታይ ጨዋታ አሸንፎ የነበረው ድሬዳዋም ለመጀመርያ ጊዜ ሽንፈት ቀምሷል፡፡ 09:00 በአበበ ቢቂላ በተደረገው ጨዋታ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ባልተጠበቀ ሁኔታ መከላከያን በመርታት የመጀመርያ 3 ነጥብ ማግኘት ችሏል፡፡ ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ ጠንካራ አጀማመር ያደረገው መከላከያ በቡና የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡

የምድቡ 5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከቅዳሜ ጀምረው መካሄድ ሲጀምሩ አዳማ ላይ በ10:00 አዳማ ከተማ ከ ደደቢት የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ ሁለቱም በ4 ጨዋታ 12 ነጥብ በመያዝ ምርጥ አጀማመር በማድረጋቸው ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የግብ አዳኞቹ ሎዛ አበራ እና ሴናፍ ዋኩማ ልዩነት ፈጣሪነት የሚታየበትም ይሆናል፡፡

መከላከያ ከ ጥረትን ቅዳሜ በ09:00 አአ ስታድየም ሲያስተናግድ እሁድ ድሬዳዋ ላይ በ08:00 ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና ፤ ሰኞ አአ ስታድየም ላየይ በ09:00 ቦሌ ከ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ፣ 11:30 ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የምድብ ሀ 5ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ናቸው፡፡
የምድቡ የደረጃ ሰኝጠረዥ ይህንን ይመስላል፡-

picsart_1481865393690

ምድብ ለ

የዚህ ምድብ 4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ማክሰኞ መካሄድ ሲጀምሩ አዲስ አበባ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ወደ ውድድር በመመለሳቸው አመቱ ከተጀመረ ወዲህ ሁሉም ጨዋታዎች ለመጀመርያ ጊዜ ተካሂደዋል፡፡ አዲስ አበባ በውስጥ ውዝግብ ፣ ሲዳማ ቡና ደግሞ በዝግጅት ጊዜ ማነስ ምክንያት የመጀመርያዎቹ 3 ጨዋታዎች አልፏቸዋል፡፡

ማክሰኞ 09:00 ላይ ልደታ ክ/ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማን 2-1 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ድል አሳክቷል፡፡ በዚሁ እለት 11:30 ተዋሳ ከተማን ያስተናገደው አዲስ አበባ ከተማ 2-0 ተሸንፏል፡፡ በጨዋታው አዲስ አበባ ከተማ በቂ ቅድመ ውድድር ዝግጅት አለማድረጉ እንዲቸገር አድርጎታል፡፡ ሀዋሳ ያደረጋቸውን ሶስቱንም ጨዋታዎች በድል በመወጣት አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

ረቡዕ 09:00 ላይ አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸንፎ ነጥቡን ወደ መሪዎቹ አስጠግቷል፡፡ 11:30 ላይ ቅድስት ማርያም ጌዲኦ ዲላን 4-2 በመርታት በ7 ነጥብ 3ኛ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡

picsart_1481864845169

በ4ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሲዳማ ቡና ያደረጉት ጨዋታ ያለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ባንክ ወሳኝ ተጫዋቾቹን በጉዳት ያላሰለፈ ሲሆን የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ጨዋታ ያደረጉት ሲዳማዎች ባልተጠበቀ ሁኔታ ለንግድ ባንክ ፈታኝ ተጋጣሚ ሆነው ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል፡፡

የ5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ ሲጀምሩ ሰኞ በሀዋሳ ስታድየም ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡ ንግድ ባንክ አንድ ቀሪ ጨዋታ ያለው ሀዋሳን በ1 ነጥብ በመብለጥ የምድቡ መሪ ሲሆን ሀዋሳ ካደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች ሙሉ 9 ነጥብ ማግኘት ችሏል፡፡

ቅዳሜ 11:30 አአ ስታድየም ላይ አቃቂ ቃሊቲ ከ አዲስ አበባ ሲጫወቱ ሰኞ አርባምንጭ ከ ልደታ ፣ ጌዲኦ ዲላ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ሲዳማ ቡና ከ ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ 09:00 በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ፡፡

የምድቡ የደረጃ ሰንጠረዥ ይህንን ይመስላል:-

picsart_1481865362871

Leave a Reply