በ13ኛው ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና መከላከያን በማሸነፍ ወደ መሪዎቹ ተጠግቷል፡፡
ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስና መረብን ለማገናኘት የወሰደባቸው ደቂቃ 2 ብቻ ነበር፡፡ አስቻለው ግርማ ከግራ መስመር የተሸገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ኢትዮጵያ ቡናን መሪ የምታደርግ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
ከግቧ መቆጠር በኋላ በመጠኑ ጫና የፈጠሩት መከላከያዎች ፍፁም ቅጠት ምት ቢያገኙም የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሽመልስ ተገኝ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡
በ31ኛው ደቂቃ ዳዊት እስጢፋኖስ ከመስኡድ መሃመድ የተሸገረለትን ኳስ ወደ ግብ ቀይሮ የጨዋታው የመጀመር አጋማሽ በኢትዮጵያ ቡና 2-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡
ከእረፍት መልስ ፍፁም የበላይነት የነበራቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በ48ኛ ደቂቃ የኤፍሬም አሻሞ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ውጤቱን ወደ 3-0 ከማስፋታቸው በተጨማሪ በውብ ጨዋታ እና በርካታ የግብ ሙከራዎች ደጋፊውን ሲያዝናኑ አምሽተዋል፡፡ በተለይም በአማካይ ክፍሉ የማስኡድ መሃመድ ፣ ፋሲካ አስፋው እና ዳዊት እስጢፋኖስ ጥምረት አስደማሚ ነበር፡፡
መከላከያ በ54ኛው ደቂቃ በመዳህኔ ታደሰ ግብ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርግም ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 3-1 አሸናፊነት ከመጠናቀቅ አላገደውም፡፡
በተከታታይ ጨዋታዎች ድል የቀናው ኢትዮጵያ ቡና የዛሬውን ድሉን ተከትሎ ነጥቡን ወደ 19 አሳድጎ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ መከላከያ በበኩሉ በ17 ነጥብ ወደ 5ኛ ደረጃ ወርዷል፡፡
{jcomments on}