በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን አጠናከረ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እሁድ ፣ ሰኞ እና ማክሰኞ በተደረጉ ጨዋታዎች ሲቀጥል ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮጵያ ቡና ድል ቀንቷቸዋል::

በአዲስ አበባ ስታዲየም ሐረር ቢራን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ 5-1 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ከተከታዩ ጋር ያለውን ልዩነት አስፍቷል፡፡ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ሐረር ቢራዎች ሲሆኑ ልይህ ገብረመስቀል በግንባሩ በመግጨት ሐረር ቢራን መሪ አድርጎት ነበር፡፡ የግቧን መቆጠር ተከትሎ ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱት ፈረሰኞቹ የእለቱ አንበል በነበረው አይዛክ ኢሴንዴ ግብ አቻ መሆን ቻሉ፡፡

ከግቧ መቆጠር በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአማካዩ ያሬድ ዝናቡ እና በፍፁም ገብረማርያም ሁለት ሁለት ግቦች ታግዘው 5-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፈው ተመልሰዋል፡፡

ፋሲለደስ ላይ ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው ዳሽን ቢራ ያለግብ 0-0 ሲለያይ በተመሳሳይ አሰላ ላይ አርባምንጭ ከነማን ያስተናገደው ሙገር ሲሚንቶ ያለግብ አቻ ተለያቷል፡፡

ሰኞ በተደረገው ብቸኛ ጨዋታ ኢትዮያ ቡና ኢትዮጵያ መድንን 2-1 በማሸነፍ ደረጃውን ከፍ አድርጓል፡፡

ለአደገኞቹ በመጀመርው አጋማሽ ዳዊት እስጢፋኖስ በቅጣት ምት እንዲሁም ቢንያም አሰፋ በክፍት ጨዋታ ሁለቱን ግቦች ከመረብ ሲያሳርፉ ጀማል አህመድ ለኢትዮጵያ መድን ብቸኛዋን ግብ በሁለተኛው አጋማሽ አስቆጥሯል፡፡

ማክሰኞ እለት ወደ ሀዋሳ አቅንቶ ሀዋሳ ከነማን የገጠመው ኢትዮያ ንግድ ባንክ በመሃሪ መና እና በኤልያስ ማሞ ግቦች 2-1 አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ለሀዋሳ ብቸኛዋን ግብ ተመስገን ተክሌ አስቆጥሯል፡፡

በእለቱ አዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ሌላ ጨዋታ መከላከያ እና መብራት ኃይል 1-1 አቻ ተለያይተዋል፡፡ መብራት ኃይል በራምኬል ሎክ ግብ ለረጅም ደቂቃዎች መምራት ቢችልም አማኑኤል ግደይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች መከላከያን ከሽንፈት ታድጎታል፡፡

ፕሪሚየር ሊጉን 2 ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ቅዱስ ጊዮርጊስ በ30 ነጥብ ሲመራ ንግድ ባንክ በ22 ይከተላል፡፡

{jcomments on}