የጨዋታ ሪፓርት | አዳማ ወደ ሰንጠረዡ አናት ከፍ ያለበትን ድል አስመዝግቧል 

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 6ኛ ሳምንት በሜዳው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ወልዲያ ያስተናገደው አዳማ ከተማ በሲሳይ ቶሊ ብቸኛ ግብ 1-0 በማሸነፍ ነጥቡን ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ እኩል አድርሷል፡፡

ከጨዋታው መጀመር በፊት በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት ለተለየውና የአዳማ ተወላጅ ለሆነው ለድምፃዊ ኤርሚያስ አስፋው የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡

ከጨዋታው መጀመር አንስቶ የመሀል ሜዳውን ብልጫ በመውሰድ አጥቅተው ለመጫወት ያሰቡ የሚመስሉት አዳማ ከተማዎች ገና ጨዋታው በተጀመረ በ6ኛው ደቂቃ ሱሌይማን መሀመድ ከግራ መስመር በወልዲያ የግብ ክልል ጠርዝ ላይ ይገኝ ለነበረው ሲሳይ በረጅሙ ያቀበለውን ኳስ ሲሳይ ቶሊ በግሩም ሆኔታ ከተቆጣጠረ በኃላ አጠገቡ ይገኝ የነበረውን የወልዲያ ተከላካይ አልፎ የእለቱን ብቸኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት አዳማዎች በ12ኛው ደቂቃ ፋሲካ አስፋው ያሻማውን ኳስ ታፈሰ ተስፋዬ በመዘግየቱ የተነሳ ሳይደርስባት ቀረ እንጂ መሪነታቸውን ማሳደግ ሊችሉ የሚችሉበት አጋጣሚ ነበር፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ የተወሰደባቸው ወልዲያዎች በ20ኛው ደቂቃ ያሬድ ሀሰን ከግብ ክልል ውጪ አክርሮ የመታው እና ከግቡ አግዳሚ በላይ የወጣው ኳስ የመጀመሪያ ሙከራቸው ነበር፡፡

በ31ኛው ደቂቃ የመጀመሪያዋ ግብ ከተቆጠረችበት ሂደት ጋር በሚመሳሰል መልኩ ሲሳይ ቶሊ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ታፈሰ ተስፋዬ ሚዛኑን ሊጠብቅ ባለመቻሉ ሳይጠቀምባት ቀርቷል፡፡

አዳማዎች በድጋሚ በ35ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን ኳስ ተጠቅሞ ሚካኤል ጆርጅ ታፈሰ ተስፋዬን ከግብ ጠባቂው ጋር 1-1 ቢያገናኘውም ታፈሰ የሞከራትን ኳስ ቤሌንጌ አድኖበታል፡፡

ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው በመከላከል ስራ ላይ ተጠምደው የነበሩት ወልዲያዎች በጨዋታው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ለማድረግ 42 ያክል ደቂቃዎችን ጠብቀዋል፡፡ ከማእዘን የተሻማውን ኳስ በእለቱ በወልዲያ በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አንዱአለም ንጉሴ ቢሞክርም ሱሌይማን መሀመድ ከግብ መስመር ላይ ያወጣት ኳስ በወልዲያ በኩል የምታስቆጭ ነበረች፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ በወልዲያ በኩል ፊት ላይ የነበረው አንዱአለም ንጎሴ በግሉ ከሚያደርገው ጥረት እና አልፎ አልፎ ሲሳይ ቶሊ ለማጥቃት ተስቦ ሄዶ ሲቀር ክፍት ጥሎ የሚሄደውን ቦታ ሲሳይ ሀሰን እና ዮሀንስ ሀይሉ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም በማሰብ ከሚያደርጉት ጥረት በስተቀር እጅግ ደካማ የሚባል እንቅስቃሴ ተስተውሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ 51ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ተስፋዬ የወልዲያ ተከላካዮች መዘናጋት ተከትሎ በቀኝ መስመር በኩል ሰብሮ በመግባት በቀጥታ የሞከራት ኳስ የወልዲያው ግብ ጠባቂ ቤሌንጌ በግሩም ሆኔታ አድኖበታል፡፡

በ62ኛው ደቂቃ ላይ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ሚካኤል ጆርጅ እና አዲስ ህንፃን አስወጥተው በምትካቸው ጥላሁን ወልዴን እና ሄኖክ ካሳሁንን ካስገቡ በኃላ የቡድኑ ቅርፅ ወደ 4-1-4-1 በመቀየር ተቀይሮ የገባው ሄኖክ ካሳሁን ከተከላዮቹ ፊት በመሆን ለተከላካዮቹ ሽፋን እንዲሰጥና በእለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሲሰይ ቶሊን ወደ ኃላ በመመለስ የቀኝ ተከላካይ ሚና ሲሰጠው ታፈሰ ተስፋዬ የአጥቂ መስመሩን በብቸኝነት እንዲመራ ተደርጓል፡፡

ከዚህ ቅያሬ በኃላ አዳማዎች ኳሱን ተቆጣጥረው ከማጥቃት ይልቅ ረጃጅም ኳሶችን ወደ ፊት በመጣል ለመጫወት ሞክረዋል፡፡

በአንፃሩ ወልዲያዎች ጫላ ድሪባን አስወጥተው ቁመተ መለሎውን በድሩ ኑርሁሴን በማስገባት ከመጀመሪያው በተሻለ ቀጥተኛ እግርኳስ በመጫወት የሚገኙት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ኳሶች ለመጠቀም ሞክረዋል፡፡

ከመጀመሪያው የተቀዛቀዘ በነበረው የሁለተኛው አጋማሽ የረባ የግብ ሙከራ ሳይታይበት ጨዋታው በአዳማ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ አዳማም ነጥቡን 11 በማድረስ መሪነቱን ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ጋር ተጋርቷል፡፡

 

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሸናፊ በቀለ – አዳማ ከተማ

“በተከታታይ ጨዋታ ነጥብ በመጣላችን ውጤቱን ለማስጠበቅ ስንል በሁለተኛው አጋማሽ ተከላክለን ተጫውተናል፡፡”

“በተከታታይ ሁለት አመታት ካገኘነው የሶስተኛ ደረጃ የተሻለ ውጤት በዘንድሮ የውድድር ለማምጣት እንተጋለን፡፡”

 

ንጉሴ ደስታ – ወልድያ

 

“ቡድኔ በዛሬው ጨዋታ ከምንጊዜውም የተሻለ ነበር ፤

በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በነበረብን የትኩረት ማነስ ችግር ግብ ከማስተናገዳችን ውጪ ቡድኔ የተሻለ ነበር”

“በዘንድሮው የውድድር አመት የወልዲያ እቅድ በሊጉ ላይ መቆየት ነው፡፡ ለዚህም በሜዳችን የተሻለ ነገሮችን በመፍጠር በሊጉ ለመቆየት እንጥራለን፡፡”

Leave a Reply