የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስን በይርጋለም ያስተናገደው ሲዳማ ቡና ያለግብ አቻ በሆነ ውጤት ጨዋታውን ጨርሷል፡፡ ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር የታየበት እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ የሲዳማ ቡና ፍፁም ብልጫ የታየበት ሆኖ አልፏል፡፡ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታንም ብዛት ያለው ተመልካች በስታዲየም ተገኝቶ ተከታትሏል፡፡
የጨዋታውን የመጀመሪያ አስደንጋጭ ሙከራ በፈረሰኞቹ አማካኝነት የተደረገ ነበር፡፡ በአምስተኛው ደቂቃ ከግቡ ቅርብ ርቀት ኳስን ያገኘው ሳላዲን ሰዒድ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ሳላዲን በደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ሙከራዎች ከበኃይሉ አሰፋ በግሩም ሁኔታ የተቀበላቸውን ኳሶች ተጠቅሞ ቢያደርግም ግብ ማስቆጠር አልቻለም፡፡ በተለየ በ10ኛው ደቂቃ የሳላዲንን ሙከራ የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ ለዓለም ብርሃኑ አምክኖበታል፡፡ በተቃራኒው ግብ በ13ኛው አዲስ ግደይ ከረጅም ርቀት የሞከረው ኳስ የግቡን ቋሚ ለትሞ ተመልሷል፡፡ በ24ኛው ደቂቃ ፀጋዬ ባልቻ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ በረከት አዲሱ ወደ ግብ ሞክሮ አሁንም የግቡ ቋሚ መልሶበታል፡፡
በመጀመረያው አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች በፍጥነት ወደ ግብ መድረስ ቢችሉም ደካማ በፊት መስመር የነበረባቸው የአጨራረስ ድክመት ያለግብ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ አስገድዷቸዋል፡፡
ከዕረፍት መልስ ባለሜዳዎቹ በኳስ ቁጥጥርም ይሁን በግብ ሙከራ ከእንግዶቹ ተሽለው ታይተዋል፡፡ በ63ኛ ደቂቃ ፀጋዬ ያሻማውን የማዕዘን ምት ሮበርት ኦዶንካራ በአግባቡ ማውጣት ሳይችል ቢቀርም በቅርብ ርቀት የነበረው ፍፁም ተፈሪ ኳሷን በሚያስገርም መልኩ በግብ አናት ላሰዷታል፡፡ የፈረሰኞቹ የተከላካይ ሰፍራ ተጫዋቾች ከሲዳማ ቡና አጥቂዎች የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት በመመከት በኩል ተሽለው ታይተዋል፡፡ በ71ኛው ደቂቃ አዲስ ከኦዶንካራ ጋር ቢገናኝም ዕድሉን ሳይጠቀምበት ኳሶ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ስድስት ደቂቃዎች ሲቀሩት አሁንም በድጋሚ አዲስ ወደ ግብ ቢሞክርም ሮበርት ሙከራውን አምክኖበታል፡፡
በአንድ ነጥብ ብቻ የሚለያዩት ሁለቱ ክለቦች ጨዋታቸውን 0-0 ሲጨርሱ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁንም በሲዳማ ቡና በፕሪምየር ሊጉ ግንኙነታቸው ያለመሸነፍ ጉዞውን ማስቀጠል ችሏል፡፡
የአሰልጣኞች አሰተያየት
አለማየሁ አባይነህ- ሲዳማ ቡና
“የኳስ ፍሰቱ በሁለታችንም በኩል ጥሩ ነበር፡፡ ወደ ግብ በመድረስም እኛ የተሻልን ነበርን፡፡ እነሱ ረጅም ኳስን ይጠቀማሉ፡፡ ልጆቼ የነገርኳቸውን ተግብረውልኛል፡፡ ጊዮርጊስ ረጅም ኳስን ይጫወታል፡፡ ስለሆነም ሁለቱን ተከላካዮቼን ቆመው እንዲጫወቱ አድርጊያለው፡፡ ጊዮርጊስ ልምድ ያለው ቡድን ነው ፤ ስለሆነም ማሸነፍ እንችል ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙ ኳሶችን አምክነናል፡፡ እንደአማራጭ ያሰብነው ግን ተሳክቷል፡፡”
ፋሲል ተካልኝ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
“በእኛ በኩል ጨዋታውን ማሸነፍ እንፈልግ ነበር፡፡ በመጀመሪያው 45 ብዙ ኳሶችን አምክነናል፡፡ በሁለተኛው 45 ደግሞ እነሱ ተጭነው ለመጫወት ሞክረዋል፡፡ ስለሆነም እኩል ለእኩል መውጣታችን መጥፎ አይደለም፡፡ ቶሎ ወደ አሸናፊነት መመለስ አለብን፡፡ በሶስት ተከታታይ ጨዋታ ያለማሸናፋችንን ቶሎ እንገመግመዋለን፡፡ ደካማ የምንላቸው ቦታዎች ላይ ጠንክረን እንሰራለን፡፡ በሚቀጥለው ጨዋታ ተስፋ አደርጋለሁ ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን፡፡ ግን ዕኩል በመውጣታችን ደስ አላለንም፡፡ እነሱም ጥሩ ተጫውተዋል፡፡ እኛም እንደዛው ፤ ግን መጥፎ ውጤት አይደለም፡፡”