የጨዋታ ሪፖርት | ፋሲል ከተማ 1-1 ሀዋሳ ከተማ

6ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ እና ክልል ስታዲየሞች ላይ ቀጥሎ ሲደረግ ጎንደር ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው ፋሲል ከተማ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ነጥብ ጥሏል፡፡

ጨዋታው እንደተጀመረ ሁለቱም ቡድኖች ኳሱን ለመቆጣጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ በጨዋታው አካላዊ ጉሽሚያዎች ሲፈፀሙ ቢስተዋልም የዕለቱ ዳኛ በአግባቡ ነገሮችን ለመቆጣጠር ጥረት አድርገዋል፡፡

ፋሲል ከተማዎች ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ለማግኘት የፈጀባቸው 13 ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ የሃዋሳ ከተማ ተከላካዮች በሰሩት ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት በሰኢድ ሁሴን አማካኝነት ተሻምቶ የሃዋሳ ከተማው ተከላካይ ደስታ ዮሃንስ ራሱ መረብ ላይ አስቆጥሯል፡፡

ሀዋሳ ከተማዎች ጎል ከተቆጠረባቸው በኃላ የተሻለ የተንቀሳቀሱ ሲሆን አቻ ለመሆንም የፈጀባቸው 10 ደቂቃ ብቻ ነው፡፡ በ26ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ሃይማኖት ወርቁ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ክለቡን አቻ አድርጓል፡፡

ሃዋሳ ከተማዎች የአቻነት ግባቸውን ካስቆጠሩ በኃላ በተደጋጋሚ ወደ ፋሲል ከነማዎች የግብ ክልል በመሄድ ተጨማሪ ጎሎችን ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ሳይሳካላቸው የመጀመሪያው አጋማሽ አንድ ለአንድ በሆነ ውጤት ተጠናቆ ሁለቱም ቡድኖች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ፋሲሎች ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን የቡድኑ ዋነኛ አጥቂ ኤዶም ሆሮሶውቪ በ71ኛው ፣ 77ኛው እና 86ኛው ደቂቃ በጭንቅላት በመግጨት የሞከራቸው ኳሶች ለግብነት የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሃዋሳዎች ያገኙትን አንድ ነጥብ ላለማጣት በጥንቃቄ ተከላክለው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡

በእለቱ በሃዋሳ ከተማ በኩል በርካታ ኳሶችን በማዳን ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳህ ለሃዋሳ አንድ ነጥብ ማግኘት ዋነኛ ተጠቃሽ ተጨዋች ነው፡፡

ከጨዋታው በፊት እና በኃላ የፋሲል ከተማ ደጋፊዎች ሞቅ ባለ ድባብ ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ሲስተዋል በተለይ ከጨዋታው በኃላ ለሃዋሳ ከተማ ተጫዋቾች ሲያጨበጭቡም ታዝበናል፡፡

በእለቱ የተሰበሰበው የስታዲየም የመግቢያ ክፍያ ሙሉ ለሙሉ የክለቡ የደጋፊ ማህበር እና የክልሉ መስተዳድር በመነጋገር በኩላሊት ህመም ለሚሰቃየው ጥበበ ሰለሞን ለተባለ የ23 ዓመት የፋሲል ከተማ ደጋፊ እንዲሆን መወሰኑን ከጨዋታው በኃላ የደጋፊ መሃበሩ ስራ አስፈፃሚዎች ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ በባህር ዳር ዩንቨርስቲ የአምስተኛ አመት የኢንጅነሪንግ ተማሪ የሆነው ጥበበ ሰለሞንን ወጪ ለመሸፈን ማህበሩ ጥረት እያደረገ ሲሆን የክለቡ ተጫዋቾችም 10,000 ብር አዋጥተው መለገሳቸውንም ሰምተናል፡፡

2 Comments

  1. ፋሲል እናመሠግናለን ሀዋሳ ስትመጡ በጥሩ ሁነታ እንቀበላቸዋለን

Leave a Reply