የጨዋታ ሪፖርት | ደደቢት ኤሌክትሪክን በማሸነፍ የመሪዎቹን ፉክክር ተቀላቅሏል

 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት 09:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ ደደቢት ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-0 በማሸነፍ የመሪነት ፉክክሩን ማጠናከር ችሏል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ደደቢቶች ለአጥቂዎቹ በሚላኩ ረጅም ኳሶች ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው ኳስን ለመቆጣጠር እና ከቆሙ ኳሶች በሚፈጠሩ ዕድሎች ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውሏል፡፡ በ5ኛው ደቂቃ ኤሌክትሪኮች ከማዕዘን ምት ያሻሙት ኳስ በእጅ ተነክቷል በሚል ፍፁም ቅጣት ምት እንዲሰጣቸው ቢጠይቁም ዳኛው በዝምታ አልፈዋል፡፡

በ12ኛው ደቂቃ የደደቢቱ ተከላካይ አይናለም ሀይሉ በአለምነህ ግርማ ላይ ከኋላ ሁለት እግሮቹንም ተጠቅሞ በመጥለፍ አደገኛ ጥፋት በመፈፀሙ በቀጥታ ቀይ ከሜዳ የተወገደ ሲሆን ደደቢትም ቀሪ 78 ደቂቃዎችን በ10 ተጫዋች ለመጫወት ተገዷል፡፡ ኤሌክትሪክ ያለውን የቁጥር ብልጫ በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር በሙሉዓለም ጥላሁን፣ ፍፁም ገብረማርያም እና አሸናፊ ሽብሩ አማካኝነት ሙከራዎች ቢያደርጉም ጥረታቸው ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡

በጨዋታው 59ኛ ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከ30 ሜትር ርቀት አካባቢ የመታውን ቅጣት ምት ግብ ጠባቂው ሱሌይማኔ አቡ ሲመልሰው አስራት መገርሳ አግኝቶ በቀላሉ በማስቆጠር ደደቢትን መሪ አድርጓል፡፡ በግቡ መቆጠር የተደናገጡት ኤሌክትሪክ ተረጋግተው ወደጨዋታው ከመመለሳቸው በፊት በ64ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ የአወት ገብረሚካኤልን ስህተት በመጠቀም ልዩነቱን ማስፋት ችሏል፡፡ ግቡም ጌታነህ ከበደ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠረው 6ኛ ግብ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ከግቦቹ መቆጠር በኋላ ኤሌክትሪክ ግብ አስቆጥሮ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ወደፊት ተጭኖ ለመጫወት ፤ ደደቢት ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ልዩነቱን የበለጠ ለማስፋት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ተጨማሪ ጎል ማግኘት ሳይችሉ ጨዋታው በደደቢት 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ደደቢት ጨዋታውን በማሸነፉ ያለውን ነጥብ 11 ማድረስ የቻለ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ በግብ ክፍያ ተበልጦ 2ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡ ተሸናፊው ኤሌክትሪክ በበኩሉ በ4 ነጥብ እና 3 የግብ ዕዳ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ይገኛል፡፡

 

የአሰልጣኞች አስተያየቶች

picsart_1482086804177

አስራት ሃይሌ – ደደቢት

“ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡ በእግርኳስ እንቅስቃሴ ውስጥ ተጫዋች በቀይ  ሊወጣብህ ይችላል፡፡ እንደ አሠልጣኝ እንደዚህ ያሉ ነገሮች ቢያጋጥሙ ብለህ የምትሰራቸው ስራዎች አሉ፡፡ ስለዚህ እኛ በጎደሎም ብንጫወት እንዴት ማሸነፍ እንችላለን ብለን አስቀድመን በግል ልምምድ ላይ እንሰራለን፡፡ የዛሬው እንቅስቃሴያችን በልምምድ ላይ የሰራነውን በሜዳ ላይ ያሳየንበት ነበር፡፡ ሙሉ በሙሉ እንደምናሸንፍም እርግጠኛ ነበርኩ፡፡”

“ደደቢት እኔ የምፈልገው እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል ለማለት ገና ብዙ የሚቀሩ ነገሮች አሉ፡፡ አኔም በዋና አሠልጣኝነት ቡድኑን ከያዝኩኝ ገና 15 ቀን አልሆነኝም፡፡ ቡድኑ በአካል ብቃት ትንሽ ደከም ያለ ነበር፡፡ ቡድናችን ቅርፅ አልነበረውም፡፡ ነገርግን አሁን ቅርፅ ይዟል፡፡ በማጥቃት እና መከላከል ላይ እንዴት መሄድ እንዳለባቸው እያሳየኋቸው ነው፡፡”

picsart_1482086845665

ብርሃኑ ባዩ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ

“ያገኘናቸውን የግብ ዕድሎች አለመጠቀም ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ ከመጀመሪያው ጨዋታ ጀምሮ ለጎል የቀረቡ በርካታ ኳሶችን እንፈጥራለን፤ እነዛን ኳሶች ግን እንስታለን፡፡”

ደደቢቶች ያሸነፉን የጨዋታ ብልጫ ኖሯቸው አይደለም፡፡ ተጫዋቾች በግል በሚፈጥሯቸው ስህተቶች ምክኒያት ግቦች ተቆጠሩብን፤ ይህም በተጫዋቾቹ ላይ የስነ ልቦና ችግር ፈጥሮ በሙሉ አቅማቸው መጫወት እንዳይችሉ አድርጓቸው ነበር፡፡”

“የስብስብ ጥበት አለብን፤ አሁን 22 ተጫዋቾች ነው ያሉን፡፡ 2 ተጫዋቾች በቅጣት መሰለፍ አልቻሉም፡፡ በመከላከሉ ላይ ባለው ክፍተት ምክንያት አማካዩን አዲስ ነጋሽ ወደ ተከላካይ ክፍል ወስጄ ለማጫወት ተገድጃለሁ፡፡ ይህ ክፍተት ከመጀመሪያው ጀምሮ የነበረ የማውቀው ችግር ነው፤ ይህን የሚቀርፍልን ተጫዋች ገበያ ላይም ማግኘት አልቻልንም ነበር፡፡”

“በየጨዋታው እያጣነው የምንወጣው ነጥብ በተጫዋቾች ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ሆኖም ግን በአጥቂ እና ተከላካይ መስመር ያሉ ችግሮችን መፍታት ከቻልን የተቀናጀ እና ኳስ ይዞ መጫወት የሚችል አቅም ያለው ቡድን ስላለን ያገኘናቸውን ኳሶች መጠቀም እንድንችል የሚረዳን ሰው ካገኘን ከኋላም እንደዚሁ አንድ ሰው ከጨመርን ውጤት ማምጣት እንችላለን፡፡ ገና ነው፤ ተስፋ የሚያስቆርጥ ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡”

 

Leave a Reply