የፕሪሚየር ሊጉ 12ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀምራል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በክልል እና አዲስ አበባ በሚደረጉ የ12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቀጥሎ ይውላል፡፡

የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ3 ተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች መልስ በሜዳው ሀረር ቢራን ያስተናግዳል፡፡ ፈረሰኞቹ ያለፉትን 14 ተከታታይ የሊግ እና የሲቲካፕ ጨዋታዎችን በሙሉ በድል የተወጡ ሲሆን ዛሬም ሀረር ቢራን አሸንፈው የነጥብ ልዩነታቸውን ከማስፋት የሚያግዳቸው ያለ አይመስልም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀሙስ ሀዋሳ ከነማን 1-0 የረታ ሲሆን ሀሀር ቢራ ሰኞ በአርባምንጭ 2-1 ተሸንፎ ተመልሷል፡፡

በ9 ሰአት በአሰላ ደራርቱ ስታዲየም ሙገር ሲሚንቶ አርባምንጭ ከነማን ያስተናግዳል፡፡ በሊጉ 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት አርባምንጮች ይበልጥ መሪዎቹን ለመጠጋት የዛሬውን የአሰላ ፈተና በብቃት መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ያለፉትን 2 ተከታታይ ጨዋዎች የተሸነፈው ሙገርም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ብርቱ ፍልሚያ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ዳሽን ቢራ በፋሲለደስ ስታዲየም ሲዳማ ቡናን የሚያስተናግድበት ጨዋታም ዛሬ ከሚደረጉ መርሃግብሮች አንዱ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና 2 ጊዜ የተሸነፈው ዳሽን ዛሬ በሜዳው ሁለተኛ ድሉን ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ ሲዳማ ቡና በበኩሉ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድል ለማስመዝገብ ይፋለማል፡፡

ሊጉ ሰኞ እና ማክሰኞ በሚደረጉ ጨዋታዎችም ይቀጥላል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ