ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ የአፍሪካ ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል

የቶታል ቻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣርያ ዙር ድልድል ዛሬ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ይፋ ሆኗል፡፡

በቻምፒየንስ ሊጉ የሚካፈለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅድመ ማጣርያው የሲሸልሱ ቻምፒዮን ኮት ዲ ኦርን ይገጥማል፡፡ የሁለቱ ክለቦች የመጀመርያ ጨዋታ በቪክቶርያ ከየካቲት 3-5 ባሉት ቀናት ሲደረግ የመልሱ ጨዋታ ከሳምንት በኋላ ይደረጋል፡፡

ኮት ዲ ኦር ከ2 አመታት በፊት በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ከሌላው የኢትዮጵያ ክለብ ደደቢት ጋር ተጫውቶ 5-2 በሆነ አጠቃላይ ውጤት ተሸንፎ ከቅድመ ማጣርያው መሰናበቱ የሚታወስ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ዙር ኮት ዲ ኦርን አሸንፎ ካለፈ የኮንጎ ብራዛቪሉ ኤሲ ሊዮፓርድስ እና የካሜሩኑ ዩኤምኤስ ዴ ሉም አሸናፊን በ1ኛው ዙር ይገጥማል፡፡

በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው የሚሳተፈው መከላከያ በቅድመ ማጣርያው የካሜሩኑ ዮንግ ስፖርትስ አካዳሚን ያገኛል፡፡ ጦሩ የመጀመርያውን ጨዋታ ከየካቲት 3-5 ባሉት ቀናት አዲስ አበባ ላይ ጨዋታውን ሲያደርግ ከሳምንት በኋላ የመልሱን ጨዋታ ባሜንዳ ከተማ ላይ ያደርጋል፡፡ መከላከያ ይህን ዙር ካለፈ የቱኒዚያው ሲኤስ ሴፋክሲየንን የሚገጥም ይሆናል፡፡

ካፍ የቻምፒየንስ ሊጉ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫውን አሰራር ዘንድሮ የቀየረ ሲሆን ወደ ምድብ ድልድሉ የሚገቡት ክለቦች ብዛት ከ8 ወደ 16 አድጓል፡፡ ክለቦቻችን በቅድመ ማጣርያው እና 1ኛው ዙር ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈው ካለፉ ወደ ምድብ ድልድሉ ሲካተቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኮት ዲ ኦርን አሸንፎ በ1ኛ ዙር ተጋጣሚው የሚሸነፍ ከሆነ ወደ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ወርዶ ይጫወታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *