የሼክ መሀመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታዲየም ጥር 6 በይፋ ይመረቃል

በወልዲያ ከተማ የተገነባው የመሃመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታዲየምን የተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ በ8፡00 ሰዓት በሸራተን አዲስ ተሰጥቷል፡፡

የፊፋ እና የአለማቀፉን የአትሌቲክ ማህበር ደረጃን የጠበቀ መሆኑን የተነገረለት ስታዲየም 25155 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም እንዳለው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡

የስታዲየሙን ግንባታ ሙሉ ወጪ ትውልደ ኢትዮጵያዊው የሳውዲ አረቢያ ባለሃብት ሼክ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ የሸፈኑ ሲሆን ለስታዲየሙ ግንባታ በአጠቃላይ 567,890,000 ብር ወጥቶበታል ተብሏል፡፡ በመግለጫው ላይ የተገኙት የሜድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አረጋ ይርዳው የስታዲየሙ ግንባታ 95 በመቶ የሚሆነው ግበአት የተገኘው ከሃገር ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

” ወልዲያ ከተማ የተሰራው ስታዲየም ስሙ ሼክ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታዲየም ነው የሚባለው፡፡ ስሙን የሰጠው ህብረተሰቡ ነው፡፡ ይህ ስታዲየም የተሰራው በሼክ መሃመድ ገንዘብ ነው፡፡ ከዚህ በኃላ ግን ስታዲየሙ የኢትዮጵያዊያን ሃብት ነው፡፡ ለህዝብ፣ ዞኑ እና ለከተማ አስተዳደሩ ነው የሚሰጠው፡፡ ሚድሮክ በቀጣዩ ስራ ላይ የለበትም፡፡ ስራውን የሰራው እኔ የምመራቸው 25 የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎቹ አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አስሩን በማስተባበር ሃገር በቀል የሆነ ልዩ ስታዲየም ነው የሰራነው፡፡ ልዩ የሚያደርገው ምንአልባትም ከ95 በመቶ በላይ ለግንባታው አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች ከዚሁ ከሃገራችን ያገኘነው ነው፡፡ መቶ በመቶ በኢትዮጵያዊውን የተገነባ ስታዲየም ነው፡፡ ” ብለዋል ዶክተር አረጋ፡፡

picsart_1482343756938

ስታዲየሙ በ177,000 ሜትር ካሬ ላይ ያረፈ ሲሆን የእግርኳስ እና መሮጫ መም ብቻ ሳየሆን የኦሎምፒክ መመዘኛን ያሟላ የመዋኛ ገንዳ፣ የቅርጫት ኳስ ሜዳ፣ የእጅ ኳስ፣ መረብ ኳስ እና ሁለት የሜዳ ቴኒስ ሜዳዎችን ከእንግዳ ማረፊያ ጋር ይዟል፡፡ 10 በሮች ያሉት ስታዲየሙ ሙሉ የፀሃይ መጠለያ አለው፡፡ 8 ለጋዜጠኞች ብቻ የተዘጋጁ ድምፅን መከላከያ የተገጠመላቸው ክፍሎች፣ የአራት የቡድኖች በአንድ ግዜ ሊያስተናግድ የሚችሉ ክፍሎች አለው፡፡ የመጫወቻ ሜዳው ከውጭ ሃገር ሳር ጋር የተዳቀለ ነው ተብሏል፡፡ ስታዲየሙ 156 መብራቶች አሉት፡፡ የመብረቅ መከላከያ፣ የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት፣ የውድድር ውጤት ማሳያ ሰሌዳዎች፣ በዝናብ ጊዜ መጫወት እንዲያስችል የሰረገን ውሃ ወደ ውጪ የሚያስተላልፍ ደረጃውን የጠበቀ የተፋሰስ ቦይ እንዲሁም የመኪና ማቆሚያ ቦታ አለው፡፡ ግንባታው የወሰደው አራት ዓመት ተኩል ነው፡፡ ግንባታውን ያካሄደው ሁዳ ሪልእስቴት ቢሆንም ሌሎች 9 የሚድሮክ ኩባንያዎችም ተሳትፈዋል፡፡

picsart_1482343684124

የምረቃው ስነ-ስርዓት ጥር 6 እንሚደረግ የተጠቆመ ሲሆን በመክፈቻው ስነ ስርዓት ላይ አዲስ አበባ እና ወልዲያ የሚገኙት የመቻሬ ቡድኖች ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ ጥር 7 ወልዲያ ድሬዳዋ ከተማን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ11ኛው ሳምንት ጨዋታ የስታዲየሙ የመጀመሪያ የነጥብ ጨዋታ ይሆናል፡፡

Leave a Reply