የጋቶች ፓኖም ጉዳይ . . .

የኢትዮጵያ ቡና እና የዋሊያዎቹ አማካይ ጋቶች ፓኖም በክለቡ ያለው የውል ዘመን በመጪው ሚያዚያ ይጠናቀቃል፡፡ ጋቶች በኢትዮጵያ ቡናም ይሁን በብሄራዊ ቡድን ቁልፍ ተጫዋች ሲሆን ከአደገኞቹ ጋር የውል ማራዘሚያ ድርድር በወኪሉ ዴቪድ በሻ በኩል መደረጉን ሶከር ኢትዮጵያ ማወቅ ችላለች፡፡

የጋቶች ወኪል ዴቪድ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደሰጠው አስተያየት ከሆነ ተጫዋቹ በኢትዮጵያ ቡና ያለው ቆይታ አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡ “ከኢትዮጵያ ቡና አመራሮች ጋር ስለውል ማራዘሙ ጉዳይ አውርተን ነበር፡፡ ቢሆንም ድርድሩ የተሳካ አልነበረም፡፡ የጋቶች ውል የሊግ ጨዋታዎች ከመጠናቀቃቸው በፊት ስለሚጠናቀቅ የውል ማራዘሙን እንደመጀመሪያ ዕቅድ ይዘን ነበር፡፡ ቡና ያቀረበው የአንድ ዓመት ተኩል የውል ግዜ ሲሆን ጋቶች በውጪ ሃገር የመጫወት ዕድል ካገኘ የመልቀቅ ጉዳይ ላይ ከስምምነት መድረስ አልቻልንም፡፡”

ጋቶች በሃገር ውስጥ ከሚገኙ ክለቦች ጋር ስሙ በተወሰነ ደረጃ ቢያያዝም ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ክለቦች ስማቸው ተነስቷል፡፡ “አሁን ላይ ስለዝውውር ማውራት አንችልም፡፡ የዝውውር መስኮቱ ዝግ ነው፡፡ የተወሰኑ ያየናቸው ነገሮች አሉ፡፡ አሁን ላይ መካከለኛው ምስራቅ ነው ካታር ነው ማለት አልችልም፡፡ በዚህ ላይ ተጨማሪ አስተያየት መስጠት አልችልም::” ብሏል ዴቪድ፡፡

ጋቶች የኢትዮጵያ ቡና 2ኛ አምበል ሲሆን በክለቡ የወጣት ቡድን ስር ያለፈ ተጫዋች ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2008 በግሉ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻለ ሲሆን ለዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ እና በቻን ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ከሌሶቶ እና ኬንያ ጋር ባደረጉበት ወቅት ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ በ2009 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ቡናው መስኡድ መሃመድ ባልነበረበት ጨዋታዎች ላይ ክለቡን በአምበልነት የመራ ሲሆን በሁለተኛው ሳምንት ከመከላከያ ጋር 2 አቻ ሲለያዩ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ አስቆጥሯል፡፡

 

(ይህ ፅሁፍ ትላንት በሬድዮ ፕሮግራማችን ላይ ካስደመጥነው የተወሰደ ነው)

Leave a Reply