በፊፋ የሃገራት ደረጃ ኢትዮጵያ 3 ደረጃዎች አሻሽላለች

የአለማቀፉ የእግርኳስ የበላይ አካል ፊፋ የ2016 የመጨረሻ የሃገራት ደረጃን ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያም በህዳር ወር ከነበራት 291 ነጥቦች በአምስት ጨምራ 296 ነጥቦች በመሰብሰብ ከነበረችበት 115ኛ ወደ 112ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች፡፡

ኢትዮጵያ በነሃሴ ወር መጨረሻ በአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ የመጨረሻ ጨዋታ ሲሸልስን 2-1 ሃዋሳ ላይ ካሸነፈች በኃላ አንድም ጨዋታ ማድረግ አልቻለችም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ተመሳሳነጥብ የሰበሰበችው ቦትስዋና ከኢትዮጵያ ጋር 112ኛ ደረጃን ተጋርታለች፡፡

ከአፍሪካ ሃገራት ሴኔጋል በደረጃው ላይ ቀዳሚ ስትሆን የ2015 የአፍሪካ ቻምፒዮኗ ኮትዲቯር እና የሰሜን አፍሪካዎቹ ቱኒዚያ፣ ግብፅ እና አልጄሪያ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ ከሴካፋ ዞን ሃገራት ደግሞ ሰኞ ለአፍሪካ ዋንጫው ጠንካራ ዝግጅት የጀመረችው ዩጋንዳ ቀዳሚ ሆኗለች፡፡ ዩጋንዳ ከአለም 72ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻለች ሲሆን ኬንያ 89ኛ ሩዋንዳ 92ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅዋ ጋቦን 110ኛ ላይ ተቀምጣለች፡፡ አንጊላ፣ ባሃማስ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ጅብላታር፣ ሶማሊያ እና ቶንጋ ያለምንም ነጥብ የመጨረሻው 205ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገደዋል፡፡

የ2016 የመጨረሻ ወር የሃገራት ደረጃ መምራት የቻለችው አርጀንቲና ነች፡፡ የደቡብ አሜሪካ የአርጀንቲና ባላንጣ ብራዚል ሁለተኛ እንዲሁም ጀርመን ሶስተኛ ሲሆኑ ቺሊ፣ ቤልጂየም፣ ኮሎምቢያ፣ ፈረንሳይ፣ ፓርቹጋል፣ ዩራጉአይ እና ስፔን እስከ10 ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

የሴቶች ደረጃ በነገው ዕለት የሚወጣ ሲሆን በነሃሴ ወር 105ኛ የነበሩት ሉሲዎቹ የደረጃ መሻሻል ሊያሳዩ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሉሲዎች በሴቶች የሴካፋ ዋንጫ መስከረም ወር ላይ ጂንጃ ዩጋንዳ በተዘጋጀበት ወቅት ሶስተኛ ሆነው ውድድራቸውን ማጠናቅ ችለዋል፡፡

Leave a Reply