የሽመልስ በቀለ ግብ ፔትሮጀትን ወደ ቀጣዩ ዙር አሳልፏል

የግብፅ ዋንጫ ጨዋታዎች ዕረቡ ሲጀመሩ ዛሬ በአል ስዌዝ ስታዲየም አስዩትን ያስተናገደው ፔትሮጀት 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ የማጣሪያ ዙር ማለፉን አረጋግጧል፡፡

የፔትሮጀትን የድል ግብ ኢትዮጵያዊው ሽመልስ በቀለ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ከጉዳት መልስ ለክለቡ በመጫወት ላይ የሚገኘው የአጥቂ አማካዩ ሽመልስ ክለቡ ወደ ሁለተኛው ዙር እንዲያልፍ ያስቻለችውን ግብ በ34ኛው ደቂቃ በግንባሩ በመግጨት ነው ያስቆጨረው፡፡ አስዩቶች በፔትሮጀት የሜዳ ክልል ላይ ጫናን ፈጥረው ለመጫወት ቢሞክሩም ከመሸነፍ ሊድኑ ግን አልቻሉም፡፡ በጨዋታው ላይ ሽመልስ ከአስዩት ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ባለመግባባት የፈጠሩትን ስህተት ተጠቅሞ የሞከረው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡

ሽመልስ በሳለፍነው ዕሁድ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ፔትሮጀት ከኢስማኤሊ ጋር 1-1 በተለያየበት ጨዋታ ላይ ሙሉ 90 ደቂቃ መጫወት ችሏል፡፡ ፔትሮጀት በሊጉ በ25 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ከወዲሁ በግብፅ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ተፋላሚነቱንም አረጋግጧል፡፡

የኡመድ ኡኩሪው ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ከኤፍሲ ማስር ጋር በግብፅ ዋንጫ የመጀመሪያ ዙር ካይሮ በሚገኘው አል ሰላም ስታዲየም ጨዋታውን ያደርጋል፡፡ ኤል ሃርቢ ዕረቡ ምሽት በግብፅ ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታ በዛማሌክ 1-0 ተሸንፏል፡፡

Leave a Reply