በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርስን የሚያቆመው አልተገኘም

ቅዳሜ የጀመረው የ11ኛው ሳምንት መርሃ ግብር ማክሰኞም ቀጥሎ ሲውል በደቡብ ምድር በተካሄዱ 2 ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ድል ቀንቷቸዋል፡፡

በ11 ቀናት ውስጥ 3ኛ ተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታውን ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዋሳ ከነማን 1-0 አሸንፏል፡፡ ለፈረሰኞቹ ብቸኛዋን የማሸነፍያ ግብ የመስመር አማካዩ በኃይሉ አሰፋ በቀድሞ ክለቡ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡

ቅዱስ ጊርጊስ በሀዋሳ ከነማ ላይ ያስመዘገበውን ድል ተከትሎ በ9 ጨዋታዎች ሙሉ 27 ነጥብ በመያዝ የደረጃ ሰንጠረዡን በርቀት መምራቱን ተያይዞታል፡፡

ይርጋለም ላይ ሙገር ሲሚንቶን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና የአመቱ 2ኛ ድሉን አስመዝግቧል፡፡ ሲዳማ ቡና 2-1 ባሸነፈበት ጨዋታ አግላን ቃሲም ሁለቱንም ግቦች ሲያስቆጠር ለሙገር ሲሚንቶ አኪም አካንዴ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡

እስካሁን ከ7ቱ የ11ኛ ሳምንት ጨዋዎች አምስቱ የተጠናቀቁ ሲሆን ከረጅም ጊዜ የግብ ድርቅ በኃላ ሊጉ በርካታ ግቦች ተቆጥረውበታል፡፡ ቅዳሜ መብራት ኃይል መድንን ፤ ኢትዮጵያ ዳሽን ቢራን ፤ አርባምንጭ ከነማ ሀረር ቢራን ያሸነፉበትን ጨዋታ ጨምሮ 15 ግቦች ተቆጥረዋል፡፡

የ11ኛው ሳምንት ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች የፊታችን ሀሙስ የሚካሄዱ ሲሆን ቦዲቲ ላይ ወላይታ ዲቻ መከላከያን አዲስ አበባ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደደቢትን ያስተናግዳሉ፡፡

{jcomments on}