የጨዋታ ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ድል አስመዝግቧል 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀመሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ድል አስመዝግቧል፡፡

ጨዋታው በትላንትናው እለት ከዚህ አለም በሞት ለተለየው ለጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የህሊና ፅሎት በማድረግ ነበር የተጀመረው።

የመጀመሪያው አጋማሽ በወላይታ ድቻዎች አማካይነት ሲጀመር በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ እንግዳው ቡድን ወደተጋጣሚው ሜዳ ክልል በመግባት ፈጣን እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ሞክሯል። ነገር ግን የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ለማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነበሩ። ይህ የጊዮርጊሶች የመጀመሪያ ጥቃትም መሀል ሜዳ ላይ በአብዱልከሪም ኒኪማ አማካይነት በቀኝ መስመር ለበሀይሉ አሰፋ የተላከውን ኳስ በሀይሉ ወደውስጥ ለሳላዲን ሲያሻማው ሳላዲን ሞክሮት በድቻ ተከላክዮች ተጨርፎ ወደውጪ ወጥቷል።

ከዚህኛው ሙከራ በኃላ ፈረሰኞቹ የሞከሩት ኳስ የመጀመሪያ ግብ ሆኖ ተቆጥሯል። ጎሉም በ6ኛው ደቂቃ በሀይሉ አሰፉ ከድቻዎች ግብ በግራ በኩል ያሻማው የማዕዘን ምት በናትናኤል አማካይነት ተሞክሮ ኳሱ ወደውጪ ከመውጣቱ በፊት የመስመር አጥቂው አቡበከር ሳኒ አግኝቶ ያስቆጠረው ነበር።

ከጎሉ በኃላ ጊዮርጊሶች ኳስን ተቆጣጥረው በመጫወት እና የግብ እድሎችን በመፍጠር ፤ ወላይታ ድቻዎች ከፊት በነበሩት አጥቂዎቻቸው አላዛር ፋሲካ ፣ በዛብህ መለዮ እና ፀጋዬ ብርሀኑ እንዲሁም በመሀል አማካያቻቸው መሣይ አጪሶ አማካይነት በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ጫና ለመፍጠር እና ከሚያቋርጡ ኳሶች በመነሳት እድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። ነገር ግን ድቻዎች በ19ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ እና አላዛር አንድ ሁለት ተቀባብለው በመጀመሪያው ግማሽ ላይ በቀኝ መስመር አጥቂነት ለተሰለፈው ፀጋዬ አሳልፈውለት ወደውስጥ ያሻማው እና ሮበርት ኦድንካራ ከያዘው ኳስ ሌላ ይህ ነው ሚባል ሙከራ ማረግ አልቻሉም።

ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከነበረው አብዱልከሪም ኒኪማ እና እንዲሁም ከቆሙ ኳሶች ከሚፈጠሩ እድሎች በያስር ሙገርዋ እና አበባው ቡጣቆ አማካይነት የተለያዩ ሙከራዎች አድርገዋል። ከሁሉም በላይ ግን በመጀመሪያው አጋማሽ ማገባደጃ ላይ ሳልሀዲን ሰይድ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ ለሊጉ መሪዎች የምታስቆጭ ነበረች።

ሁለተኛው ግማሽ ሲጀመር ከሁለቱ የመስመር ተመላላሾች /wing backs/ በቀኝ በኩል ተሰልፎ የነበረውን ያሬድ ዳዊትን በቀኝ መስመር ወደፊት በማምጣት በቦታው ላይ የነበረውን ፀጋዬ ብርሀኑን ደሞ በዛው ቀኝ መስመር ላይ ወደኃላ በመመለስ ለውጥ ያረጉት ድቻዎች እንደመጀመሪያው ግማሽ ሁሉ ንፁህ የግብ ማግባት አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም።

ሁለተኛው አጋማሽም እስከ 60ኛው ደቂቃ ድረስ በተቀዛቀዘ መንገድ የቀጠለ ሲሆን በ63ኛው ደቂቃ ሳልሀዲን ሰይድ ከአብዱልከሪም ኒኪማ ያገኘውን ኳስ ከወላይታ ድቻ ሳጥን ጠርዝ ላይ አክርሮ ሞክሮ ወንደሰን ገረመው ያወጣበት የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ዐይን የሚስብ ሙከራ ነበር። ሳልሀዲን 84ኛው ደቂቃ ላይ በተስፋዬ አለባቸው ተቀይሮ ከመውጣቱ 10 ደቂቃ በፊትም  በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉጨዋታ ካደረገው ያስር ሙገርዋ  የተላከለትን ኳስም ሞክሮ የድቻው ግብ ጠባቂ ወንደሰን ይዞበታል።

በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል በ67ኛው እና በ78ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይረው ወደሜዳ የገቡት አዳነ ግርማ እና ራምኬል ሎክ የቡድኑ ሁለተኛው ጎል ሲቆጠር የማቀበሉን እና የማግባቱን ሚና ተወጥተዋል። ግቡም በ79ኛው ደቂቃ ላይ ራምክል ሎክ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ በድቻዎች ሳጥን ውስጥ ይገኝ የነበረው አዳነ ግርማ በቀጥታ መቶ ሲያቆጥር የተገኘ ነበር። በዚህ እንቅስቃሴ ላይ አምስት የሚሆኑ የወላይታ ድቻ ተጨዋችቾች በመከላከል ወረዳ ላይ የነበሩ ቢሆንም አንዳቸውም አዳነን አለመቆጣጠራቸው የሚያስገርም ነበር።

ከጎሉ በኃላም በ88ኛው ደቂቃ በድጋሚ ራምኬል ሎክ  ከተመሳሳይ ቦታ ላይ አሻግሮለት አዳነ በግንባሩ ሞክሮ ግብ ጠባቂው አውጥቶበታል ። የጨዋታው የመጨረሻ ሙከራ በአቡበከር ሳኒ የመቀስ ምት የተደረገ ሲሆን ተቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ የድቻው የግራ መስመር ተመላላሽ ዳግም ንጉሴ በአስገራሚ መቀስ ምት ከግቡ መስመር ላይ አውጥቶት ቡድኑን ከሶስተኛ ጎል ታድጎታል። በዚህም የሊጉ የሰባተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

 

የአሰልጣኞች አስተያየት

ማርት ኑይ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

” ካደረግናቸው ሰባት ጨዋታዎች አራተኛ ድላችንን አስመዝግበናል። ጨዋታው ከመጀመሪያው ጀምሮ ጥሩ ነበር። እንደ እድል ሆኖም በጨዋታው መጀመሪያ ጎል ማስቆጠር ችለናል። በተቀረው የጨዋታ ጊዜም በጣም ብዙ የጎል ማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረናል። እንደውም 2-0 ትንሽ ውጤት ነው፡፡ ነገር ግን ለኔ በቂ ነው። በየጨዋታው ሁለት ግቦች ብቻ ብናስቆጥር እንኳን እስካሸነፍን ድረስ እኔ ደስተኛ ነኝ። ”

” ባለፉት ሶስት ሳምንታት ስለነባር ፣ ስለወጣት እና ስለውጪ ተጨዋቾች ብዙ ሲባል ነበር። እኔ ግን ተጨዋቾቹ ከየትም ይምጡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ኮንትራት እስከተፈራረሙ ድረስ ለቡድኑ በተገቢው መንገድ ማገልገላቸውን ነው ትኩረት የምሰጠው ”

” ሁሉም የቡድኔ ተጨዋቾች ባለፉት ሳምንታት ከነበርንበት ውጤት ማጣት በኃላ በዚህኛው ጨዋታ በሚገባ ምላሽ ሰጥተዋል። ስለተጨዋቾች የግል ብቃት መናገር አልፈልግም። ቡድኔን እንደቡድን ነው ማየው። ወደሜዳ የገቡት አስራ አራት ተጨዋቾች በሜዳ ላይ ጠንካራ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ”

“የተጋጣሚያችን የተከላካዮች ቁጥር ብዛት ብዙ ሚያሳስበኝ አይደለም። ተጋጣሚዎቻችን ሶስት አራት ወይም አምስት ተከላካዮችን ሊጠቀሙ ይችላሉ። እኛ ግን የራሳችንን ጨዋታ ነው ምንጫወተው። በመሬት ኳሶች ፣ በአየር ኳሶች ፣ በመስመሮች እና በመሀልም እናጠቃለን ፣ በማዕዘን ምቶች እና በቅጣት ምቶችም እናጠቃለን። ያንን መከላከል የነሱ ሀላፊነት ነው። እኛም የምናጠቃበትን መንገድ እንፈጥራለን ”

መሳይ ተፈሪ – ወላይታ ድቻ

“በመጀመርያው ግማሽ በተለይም በመጀመሪያው 25 ደቂቃ ኳሶች በቀላሉ እየተበላሹብን ነበር። ያለመረጋጋት ነበረብን። ከዛ በኃላ ግን የተወሰነ ተረጋግተን ኳስ ይዘን ለመጫወት ሞክረናል። ሁለተኛው አጋማሽም ላይም ተጭነን ለመጫወት ሞክረን ነበር ። ያው አልተሳካም ፤ ጊዮርጊስ አሸንፏል”

” ዛሬ ትንሽ ወረድ ብለናል፡፡ በነበረው እንቅስቃሴ ደስተኛ አይደለሁም ። ያለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ግን በነበረን እንቅስቃሴ ጥሩና ቀጣይነት ያለው ነገር አይቻለው። ነገር ግን አሁንም ማስተካከል ያለብን ነገሮች አሉ እነሱን ካስተካከልን በኃላ ግን ብዙ ጨዋታዎችን ወደ ማሸነፍ እንመለሳለን ብዬ አምናለው። ”

“በአንደኛው የመስመር አጥቂ በኩል ትንሽ የባላንስ ችግር ነበረብን። ከእረፍት መልስ እሱን ለማስተካከል ሞክረን ነበር ። ሆኖም የምንቀባበላቸው ኳሶች ላይ ስህተቶች እናበዛ ነበር ። እነዛ የኳስ ቁጥጥሮች ላይ ጥሩ ብንሆን ብዙ የጎል ሙከራዎችን እንፈጥር ነበር ብዬ አምናለው። በቀጣይ በዚህ ላይ ሰርተን እናሻሽላለን ”

” ተጋጣሚያችን ትንሽ ከሌላው ግዜ ለየት ይል ነበር። ከኃላ ኳስ መስርተው ለመጫወት ይሞክሩ ነበር።  ከዚህ አንፃር እና ከኛ ተጨዋቾችም አኳያ በተጋጣሚያችን ሜዳ ላይ ጫና ፈጥረን ለመጫወት መሞከራችን ተገቢ ነበር የተወሰኑ እድሎችንም ፈጥሮልን ነበር ።

 

Leave a Reply