የፕሪሚየር ሊጉ 11ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ጨዋዎች ይቀጥላል

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ በ9 ሰአት በተለያዩ ከተሞች 2 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲያስተናግድይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ሙገር ሲሚንቶን ያስተናግዳል፡፡

የዛሬው የሀዋሳ ከነማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ሲነሳ በሁሉም አእምሮ ዘንድ ቀድሞ የሚመጣው ክስተት አምና መቂ ላይ የተከሰተው አሳዛኝ ገጠመኝ ነው፡፡ በ2ኛው ዙር ሀዋሳ ከነማን ለመግጠም ወደ ደቡቧ መዲና የተጓዘውን ቡድናቸውን ለመደገፍ ወደ ሀዋሳ በማምራት ላይ ሳሉ በደረሰባቸው አደጋ ህይወታቸውን ያጡት 3 የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የሚያስታውሰን የዛሬው ጨዋታ በሊጉ አናት ላይ የሚገኙ ክለቦችን የሚያገናኝ በመሆኑ ድንቅ ፉክክር ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሁለቱም ቡድኖች 2 ቀሪ ጨዋታ እያላቸው የደረጃ ሰንጠረዡ 1ኛ እና 4ኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 9ኛ ተከታታይ ድሉን ካስመዘገበ ሊጉን ወደ 1 ፈረስ ብቻ ሩጫ ይቀይረዋል፡፡ በአንፃሩ ሀዋሳ ከነማ ካሸነፈ የፉክክር ሚዛኑን ነፍስ ይዘራበታል፡፡

ባለፈው ሳምንት ወደ አርባምንጭ እና ሙገር ተጉዞ ጣፋጭ ድል ያስመዘገበው የማርት ኑይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተከላካይ ክፍሉ ጥንካሬ እና በድንቅ አቋም ላይ በሚገኘው ኡመድ ኡኩሪ ግቦች ላይ እምነቱን ሲጥል ድንቅ የአጥቂ ስብስብ የያዙት ሀዋሳ ከነማዎች በድምሩ 6 ግብ ካስቆጠሩት የተመስገን ተክሌ እና አንዱአለም ንጉሴ ጥምረት ብዙ ይጠብቃሉ፡፡

የሊጉ የመጨረሻ ደረጃን የያዘው ሲዳማ ቡና የአሰላውን ሙገር ሲሚንቶ የሚያስተናግድበት ጨዋታ ሌላው የ11ኛው ሳምንት መርሀ ግብር አካል ነው፡፡

ባለፈው ቅዳሜ መብራት ኃይል መድንን ማሸነፉን ተከትሎ የሊጉን የመጨረሻ ደረጃ የተረከበው ሲዳማ ቡና ከደካማ የውድድር ዘመን ጉዞው ለማገገም የግድ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡በሊጉ ከወገብ በታች የሚገኙት ክለቦች በተቀራራቢ ነጥብ የሚገኙ በመሆናቸው ሁሉም ክለቦች እያንዳንዱን ጨዋታ በትኩረት ሊመለከቱት ይገባል፡፡

የይርጋለሙ ክለብ በ10ኛው ሳምንት በሀረር ቢራ 1-0 የተሸነፈ ሲሆን መገር ሲሚንቶም በተመሳሳይ ሀሙስ እለት በሜዳው በቅዱስ ጊዮርጊስ ከባድ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡

{jcomments on}

ያጋሩ