በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና እና መብራት ኃይል ወደ አሸናፊነት ተመለሱ

በ11ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዳሜ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ሁለት ጨዋታዎች ተካሂደው በርካታ ግቦች ተቆጥረዋል፡፡

በ8 ሰአት ኢትዮጵያ መድንን የገጠመው መብራት ኃይል በአሰልጣኝ ዮርዳን ስቶይኮቭ እየተመራ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል፡፡ ቡልጋሪያዊው አሰልጣኝ መብራት ኃይልን በፍር ድቤት ረትተው ወደ መቀመጫቸው ከተመለሱ በኋላ ቀዮቹን ለመጀመርያ ጊዜ በመሩበት ጨዋታ አዲስ ነጋሽ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም በረከት ይስሃቅ እና አብዱልከሪም ሃሰን በጨዋታ ባስቆጠሯቸው ግቦች መድንን 3-2 ረትተዋል፡፡ ለሰማያዊዎቹ ሁለቱ ን ግቦች ሰይፈዲን ሁልደር እና ተዘራ መንገሻ አስቆጥረዋል፡፡

በጨዋታው የመድኑ አማካይ ኢብራሂም ሁሴን እና የመብራት ኃይሉ አጥቂ በረከት ይስሃቅ በ 2ቢጫ ከሜዳ የተወገዱ ሲሆን ግብ አስቆጥሮ ደስታውን ማልያውን በማውለቅ የገለ ፀው በረከት የውድድር ዘመኑ 2ኛ ቀይ ካርዱ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ያለፉትን 9 ሳምንታት ካለምንም ድል የተጓዘው መብራት ኃይል ድሉን ተከትሎ ነጥቡን ወደ 8 አሳድጎ 12ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ መድን በበኩሉ ወደ 13ኛ ደረጃ ወርዷል፡፡

በጉጉት የተጠበቀው የኢትዮጵያ ቡና እና ዳሽን ቢራ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ 11 ሰአት በጀመረው ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ 0-0 ሲጠናቀ ቅ በ2ኛው አጋማሽ ዳሸን ቢራ በዮናታን ከበደ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ባለሜዳዎቹን መርቷል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኃላ ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ቢንያም አሰ ፋ እና ኤፍሬም አሻሞ አከታትለው ባስቆጠሩት ሁለት ግብ ታግዘው ጨዋታውን 2-1 አሸንፈዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ወሳኙን ጨዋታ ማሸነፉን ተከትሎ ነጥቡን ወደ 13 ሲያሳድግ ደረጃውንም ወደ 5 ከፍ አድርጓል፡፡ ባለፈው ሳምንት የመጀመርያ ድሉን ያስመዘገበው ዳሸን በበኩሉ 11ኛ ደረጃ ላይ ረገግቷል፡፡

የፕሪሚየር ሊጉ 11ኛ ሳምንት ሰኞ ፣ ማክሰኞ እና ሀሙስ በሚደረጉ ጨዋታዎች ሲቀጥል ሰኞ በ9 ሰአት አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከነማ ከ ሀረር ቢራ ፤ ማክሰኞ የሊጉ መሪ ወደ ሀዋሳ ተጉዞ በ9 ሰአት ከሃዋሳ ከነማን ይገጥማል ፤ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ከ ሙገር ሲሚንቶ ይጫወታሉ፡፡ ሀሙስ በ9 ሰአት በውድድር ዘመኑ ለመጀመርያ ጊዜ በቦዲቲ ስታዲየም የሚጫወተው ወላይታ ዲቻ መከላከያን ሲያስተናግድ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ንግድ ባንክ ከ ደደቢት በ11 ሰአት ይጫወታሉ፡፡

ያጋሩ