የጨዋታ ሪፖርት | ጅማ አባ ቡና 1-3 ፋሲል ከተማ

አዲሶቹን የፕሪሚየር ሊግ አዳጊዎች ያገናኘው የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ጨዋታ ጅማ ላይ ተካሂዶ ጅማ አባቡና በሜዳውና በደጋፊው ፊት ለፋሲል ከተማ እጁን ሰጥቷል፡፡

ጨዋታው ከትናት በስቲያ ሕይወቱ ላለፈው ለጀግናው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ  ነበር የተጀመረው፡፡

የመጀመርያው አጋማሽ እንግዳዎቹ ፋሲሎች ተሽለው በታዩበት ባለሜዳው ጅማ አባቡና ደግሞ ተዳክሞ የቀረበት ሆኖ አሳይቶናል፡፡

ጅማ አባቡናዎች በሜዳቸው እንደመጫወታቸው ጫና ፈጥረው ለመጫወት ቢሞክሩም ኳሱን ከማንሸራሸር ባለፈ ይህ ነው የተባለ ጠንካራ የጎል ሙከራ ያደረጉት በ8ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ጎል ገብቶ ያመከነው ኳስ ብቻ ተጠቃሽ ነበር፡፡ በአንፃሩ እንግዶቹ ፋሲል ከተማዎች በ3ኛው ደቂቃ በኤዶም እንዲሁም በ13ኛው ደቂቃ በናትናኤል ጋንጁላ አማካኝነት ጠንካራ የጎል ሙከራ ማድረግ ችለዋል፡፡

በ30ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አለሙ በግምት ከ17 ሜትር ርቀት የመታው ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ተቀይሮ ፋሲል ከተማን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ጅማ አባ ቡናዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያስችላቸውን አጋጣሚ መፍጠር ችለው ነበር፡፡ በ41ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ከአሜ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ የመታውና ዮሐንስ ሽኩር ያዳነበት ለዚህ ተጠቃሽ ነበር፡፡ በ45ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አባ ቡናዎች ያገኙትን የፍጹም ቅጣት ምት መሀመድ ናስር መትቶ ዮሐንስ ሽኩር በጥሩ ሁኔታ አድኖበታል፡፡ የመጀመርያ አጋማሽም በፋሲል ከተማ መሪነት ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በሁሉም ረገድ ተሽለው የቀረቡት እንግዳዎቹ ፋሲል ከተማዎች ነበሩ፡፡ በ62ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ሰለሞን ገ/መድህን ከ17 ሜትር ርቀት አክሮ መትቶ ግሩም ጎል በማስቆጠር የፋሲልን መሪነት ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኋላ ፋሲሎች ተረጋግተው በሚገባ ብልጫ ወስደውና ኳሱን በሁሉም አቅጣጫ ተቆጣጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን 75ኛው ደቂቃ ኤዶም የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ተከላካዮችን በማለፍ የፋሲል 3ኛ ጎልን አስቆጥሯል፡፡

ከዚህ ግብ በኀላ በስታድየሙ የተገኘው ተመልካች በፋሲል ከተማ አጨዋወት ተማርኮ ከፍተኛ የሆነ ድጋፉን የሰጠ ሲሆን በአንፃሩ የአሰልጣኝ ደረጄ በላይ ቡድን ላይ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሱራፌል አወል በ89ኛው ደቂቃ ቢያስቆጥርም ጅማ አባ ቡናን ከሽንፈት መታደግ አላስቻለችም፡፡ ጨዋታውም በፋሲል የጨዋታ እና የግብ የበላይነት 3-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ከ2006 የውድድር ዘመን ጀምሮ በሜዳው ሽንፈት ያላስተናገደው ጅማ አባቡና በመጨረሻም ለፋሲል እጁን ሰጥቷል፡፡

በጨዋታው ላይ ለፋሲል ከተማ አሸንፎ መውጣት ትልቁን አስተዋፅኦ ያደረገው ዮሐንስ ሽኩር ተጠቃሽ ሲሆን ከ1000 ኪ.ሜ. በላይ አቋርጠው የመጡት የፋሲል ከተማ የልብ  ደጋፊዎች የድጋፍ ድባብ አስገራሚ ነበር፡፡

 

የአሰልጣኞች አስተያየት

ደረጄ በላይ – ጅማ አባ ቡና

” በመጀመርያ እንዲህ የወረደ እነንቅስቃሴ በማሳየታችን ደጋፊዎቻችንን ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ እኔ ቡድኑን ከያዝኩ ጀምሮ በሜዳችን እንዲህ ያለ ሽንፈት አጋጥሞኝ አያቅም፡፡ ይህ በሜዳዬ የመጀመርያ ሽንፈት ነው፡፡ ”

“በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ጥሩ ነበርን፡፡ የተወሰኑ የጎል እድሎችን መፍጠር ችለን ነበር፡፡ ፍፁም ቅጣት ምትም አግኝተን አልተጠቀምንም፡፡ ”

“በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ውስጥ አልነበርንም ፤ ስለዚህም አሸንፈውን ወጥተዋል፡፡ይህ ለቀጣይ ጨዋታ ጠንክረን መጫወት እንደሚገባን መልክት ሰጥቶን አልፏል ”

ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ፋሲል ከተማ

“ልጆቼ ላይ ያለው የማሸነፍ ፍላጎት ሁሌም አስገራሚ ነው፡፡  በተከታታይ ሁለት ጨዋታ ላይ የጣሉት ነጥብ አስቆጭቷቸው ነበር፡፡ ኳሱን ተቆጣጥረን መጫወት እንዳለብን ተነጋግረን ነበር የገባነው፡፡ ያንን በማድረጋችን በጥሩ ጨዋታ አሸንፈን ወጥተናል፡፡

” ሀኪም ለአስራ አምስት ቀን እረፍት ሰጥቶኝ ነበር፡፡ ሆኖም ለምወደው ክለቤና ለህዝብ አደራ ስል መጥቼ ቡድኔን መርቻለው፡፡ የኔም መገኘት ቡድኑ ላይ የፈጠረው መንፈስ ታግዞበት አሸንፈን ወጥተናል ፡፡”

“ደጋፊዎችን ተመልከት ፤ ይሄን ሁሉ ሀገር አቋርጠው መጥተው ይደግፉናል፡፡ እኛ ያለነሱ ባዶ ነን ፤ ሁሌም ለነሱ ያለኝ አክብሮት የላቀ ነው፡፡ ”

” በቀጣይ ከኤሌክትሪክ ጋር ላለብን ጨዋታ እንጂ አሁን ስለ ዋንጫ አናስብም “

5 Comments

  1. I always pride of our club,fasil. the emprors will be champion.but I wanna recommend the players to give attention for each game.for example;our home match against hawassa tha we drew was not acceptable. keep it up the club’s gunian fans…. go a head our players

Leave a Reply