ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከውድድር ውጪ ሆነ

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ኢትዮጵያን ወክሎ እየተሳተፈ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በባህርዳር ብሄራዊ ስታዲየም ያደረገውን የመልስ ጨዋታ 2ለ1 ቢያሸንፍም በአጠቃላይ ውጤት በአልጄሪያው ኤም ሲ ኤል ኡልማ ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሆኗል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኃይሉ አሰፋ እና አዳነ ግርማ ግቦች ታግዞ 2ለ1 ቢያሸንፍም በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፈ ያለው ኤል ኡልማ ካሜሮናዊው አቤድ ኔንጎ ቴምቤድ ባስቆጠራት የቅጣት ምት ግብ ምክኒያት ከሜዳ ውጪ ባገባ በሚለው ህግ ፈረሰኞቹ ከካፍ ቻምፒየንስ ሊግ በግዜ ተሰናብተዋል፡፡ ሁለቱ ብድኖች በመጀመሪያው ጨዋታ ፋሪስ ሄሚቲ ባስቆጠራት ግብ የአልጄሪያው ክለብ 1ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

የመጀመሪያ ግማሽ

10፡00 ሰዓት ላይ ከ68ሺህ ተመልካች በላይ በተገኘበት በደመቀ ሁኔታ በተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኤም ሲ ኤል ኡልማ በፋሪስ ሄሚቲ እና ዋሊድ ደራርጃ መሪነት በመጀመሪዎቹ 5 ደቂቃዎች ወደ ግብ ለመድረስ ከፍተኛ ሙከራ ቢያደርጉም አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ተስኗቸው የመጀመሪያውን ግማሽ አጠናቅቀዋል፡፡ ለቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ሙከራ አዳነ ግርማ በግሩም ሁኔታ ቢሞክርም የግቡ ቋሚ መልሶበታል፡፡ በ10ኛው ደቂቃ አሁንም አዳነ ግርማ ከበረኛው ጋር አንድ ለ አንድ ተገናኝቶ የተፈጠረውን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ዩጋንዳዊው ብርያን ኡሞኒ የፍፁም ቅጣት ምት ውስጥ ተጠልፌያለሁ ቢልም ጂቡቲያዊው አልቢትር ፍፁም ቅጣት ምት ሳይሰጡ አልፈዋል፡፡ ምንያህል ተሾመ በመጀመሪያው ግማሽ ላይ አስደናቂ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ በተለይ የመሃል ሜዳውን በመምራት በኩል የተዋጣለት ነበር፡፡ ጨዋታውበተጀመረ በ38ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ አሰፋ ከምንያህል ተሾመ የተቀበለውን ኳስ ከ25 ሜትር ርቀት በመምታት ፈረሰኞቹን መሪ የምታደርጋቸው ግብ በድንቅ ሁኔታ ማስቆጠር ችሏል፡፡ የመጀመሪው ግማሽን ሁለቱ ቡድኖች 1ለ0 በሆነ ውጤት ጨርሰዋል፡፡

ሁለተኛ ግማሽ

በሁለተኛው ግማሽ ላይ ልክ እንደመጀመሪያው ሁሉ አሁንም ኤል ኡልማዎች በመጀመሪዎቹ 5 ደቂቃዎች ውስጥ ጫና ፈጥረው ለመጫወት ሞክረዋል፡፡ በ46ተኛው ደቂቃ ዋሊድ ደራርጃ የመጀመሪያውን የኤም ሲ ኤል ኡልማ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጓል፡፡ ኡልማዎች በተለይ በቀኝ መስመር ተጫዋቹ ኢብራሂም ቼኒሂ በኩል የማጥቃት አማራጭ ለመፍጠር ቢሞክሩም የፈረሰኞቹ ግራ ተመላላሽ ዘካሪያስ ቱጂ በአስገራሚ ሁኔታ ለመቆጣጠር ችሏል፡፡ አዳነ ግርማ በተደጋጋሚ ጊዜ ያመከናቸው የግብ ሙከራዎች በሁለተኛው ግማሽም ቀጥለው ነበር፡፡ በ68ኛው ደቂቃ ላይ አዳነ ከቅርብ ርቀት ያገኛትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት የቅዱስ ጊዮርጊስን የማለፍ ተስፋ ያለመለመች ግብ አስቆጥሯል፡፡

ከጥቂት ደቂቃዎች በኃላ በ71ኛው ደቂቃ ላይ ካሜሮናዊው አቤድ ኔጎ ቴምቤንግ በቅጣት ምት ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኋላ የኡልማዎች አማካይ ናሲም ኦሳላ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ ናሲም ያልተገባ ባህሪ በማሳየቱ ነው ከሜዳ ሊወጣ የቻለው፡፡ የተቀሩትን 18 ደቂቃዎች ኤም ሲ ኤል ኡልማዎች በ10 ተጫዋች ለመጨረስ ተገደዋል፡፡ አዳነ ግርማ የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ያገኛትን ዕድል ሳይጠቀምባት ቀርቷል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በክለቡ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ላይ ቅሬታቸው አሰምተዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስን በቅድመ ማጣሪያው ከውድድር ያስወጣው ኤም ሲ ኤል ኡልማ በመጀመሪያው ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ከጋናው አሻንቲ ኮቶኮ ጋር የሚጫወት ይሆናል፡፡

ያጋሩ