በፕሪሚየር ሊጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ዳሸን ቢራ አሸነፉ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ40 ቀናት በኃላ ለመጀመርያ ጊዜ በክልል ከተሞች ሲካሄድ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ዳሸን ቢራ እና ሐረር ቢራ ድል ቀንቷቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ አቻ ተለያይቷል፡፡

በአርባምንጭ ስታዲየም በተመልካች ረብሻ እና ውዝግብ በታጀበው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የአርባምንጭ ከነማ ጨዋታ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ለፈረሰኞቹ ግቧን ያስቆጠረው ዘንድሮ በድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው ኡመድ ኡኩሪ በ10ኛው ደቂቃ ላይ ነው፡፡ ይህች ግብ ለኡመድ 7 የሊግ ግቡ ሆና ስትመዘገብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፉት 12 የሊግ እና የሲቲካፕ ጨዋታዎች በተከታታይ 12ኛ ድሉን አስመዝግባዋል፡፡

ፋሲለደስ ላይ በተደረገው የዳሸን ቢራ እና የመብራት ኃይል ጨዋታ የዳሸንን ታሪክ የቀየረ እና መብራት ኃይልንወደ መውረድ ስጋት የመራ ወስጤት ተመዝግቧል፡፡ ዳሸን ቢራ 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ከ2001 እስከ 2005 ድረስ በመብራት ኃይል የቆየው አስራት መገርሳ ብቸኛዋን ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ዳሸን ቢራ ዘንድሮ ወደ ሊጉ ካደገ በኃላ የመጀመርያ ድሉን እና ግቡን ያስመዘገበ ሲሆን ደረጃውንም ከፍ አድርጓል፡፡

አሰላ ደራርቱ ቱሉ ስታዲየም ላይ ሙገር ሲሚንቶ ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ ካለግብ 0-0 ሲለያይ ሐረር ቢራ ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ በበረከት ገብረ-ፃዲቅ ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፎ ወጥቷል፡፡

10ኛው ሳምንት ሰኞ ቀጥሎ ሲውል በ11 ሰአት ኢትዮጵያ መድን ወላይታ ዲቻን በአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናግዳል፡፡

{jcomments on}