“በዛሬው ጨዋታ ዕድለኛ አልነበርንም” – የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሠልጣኝ ኔይደር ዶስሳንቶስ

የ2006 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በባህርዳር ከአልጄሪያው ኤም ሲ ኤል ኡልማ ጋር ባደረገው የመልስ ጨዋታ 2-1 ማሸነፍ ቢችልም ከሜዳው ውጪ ባገባ በሚለው ህግ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ሳይችል ቀርቷል። ከጨዋታው በኋላ የክለቡ አሠልጣኝ ኔይደር ዶስሳንቶስ ለጋዜጠኞች ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ ለአንባቢያን በሚመች መልኩ እንዲህ አቅርበነዋል።

ስለ ጨዋታው

“በጨዋታው ላይ ቡድኔ ጥሩ ተንቀሳቅሷል። በሁሉም ተጫዋቾቼ ደስተኛ ነኝ፤ ሁሉም የቻሉትን ሞክረዋል። አጥቅተን በመጫወትም ሁለት ግቦች ማስቆጠር ችለናል። ነገርግን ባስተናገድነው ግብ ምክኒያት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ አልቻልንም። የተቆጠረብን ቅጣት ምት በግቡ ማዕዘን 90 ዲግሪ ላይ ነው ያረፈው፤ ተጫዋቾቼ ግቡ እንዳይቆጠር ምንም ማድረግ አይችሉም ነበር። ስለዚህ በዛሬው ጨዋታ ዕድለኛ አልነበርንም ማለት ይቻላል።”

 

በጨዋታው ስለተጠቀሙበት አሰላለፍ

“በአልጄሪያ ባደረግነው የመጀመሪያ ጨዋታ ተከላክለን ውጤት ይዘን ለመውጣት ስንል በ4-4-2 የጨዋታ ሲስተም ተጠቅመናል። ዛሬ ደግሞ ግቦች አስቆጥረን ማሸነፍ ስለነበረብን ወደ 4-3-3 ለውጠነዋል። በዚህም ጥሩ መጫወት እና የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለናል።”

ተስፋዬ አለባቸው በፍፁም ገብረማርያም ተቀይሮ ስለመውጣቱ

“ኤል ኡልማዎች አንድ ተጫዋች በቀይ ስለወጣባቸው የተፈጠረውን ክፍተት ለመጠቀም አዳነ ግርማን አስወጥቶ ፍፁምን ከማስገባት ይልቅ ተጨማሪ አጥቂ መጠቀም የተሻለ አማራጭ ነበር። ለዚያ ነው ተስፋዬ አለባቸውን ያስወጣሁት።”

ስለ ባህርዳር ስታዲየም

“የባህርዳር ስታዲየም በአገሪቱ ያለው ብቸኛ ኢንተርናሽናል ደረጃውን ያሟላ ሜዳ ነው። የተነጠፈው ሳርም ለጨዋታ እጅግ አመቺ ነበር። በሜዳው ላይ ምንም ቅሬታ የለንም።”

ኤልተን ሳንቶስ እና ኡመድ ኡክሪ ቢሰለፉ ውጤቱ ይቀየር ነበር?

“ይህን ጥያቄ ልመልስልህ አልችልም። በእግር ኳስ ‘ቢሆን ኖሮ’ የሚባል ነገር የለም። በእርግጥ ሁለቱም ጥሩ ተጫዋቾች ናቸው፤ ቡድናችንን የማገዝ አቅም ያላቸው ናቸው። ግን እነርሱ ቢኖሩም እንኳን እግርኳስ ነውና የሚፈጠረውን መተንበይ አይቻልም።”

ያጋሩ