“ከ100ሺህ ያላነሰ ህዝብ ዛሬ ስታዲየም በመገኘት ጨዋታውን ተከታትሏል።” – የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ያየህ አዲስ

 

የአዲስ አበባ ስታዲየም 12ተኛውን የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮናን ለማዘጋጀት እደሳ እየተደረገለት በመሆኑ ምክኒያት ደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽንስ ካፕ የመልስ ጨዋታዎቻቸውን በባህርዳር ብሔራዊ ስታዲየም አድርገዋል። ጨዋታዎቹ በባህርዳር መደረጋቸው ለከተማው ህዝብ ስለነበረው ፋይዳ እና ተያያዥ ጉዳዮች የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ያየህ አዲስ የሰጡን አስተያየት ይህንን ይመስላል።

ባህርዳር ሁለቱን ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ማስተናገዱ ምን ጥቅም ያስገኛል?

“የባህርዳር ስታዲየም የደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የአፍሪካ ክለቦች ውድድር ጨዋታዎቻቸውን እዚህ በማድረጋቸው በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት። በመጀመሪያ በክልላችን ያለው የስፖርት እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ ትልቅ እገዛ ያደርግለታል፤ በክልሉ ያለው እግርኳስ እንዲያድግ የሚኖረው ሚና ቀላል አይደለም። ጨዋታዎቹን ለመከታተል ወደ ባህርዳር ከመጣው ተመልካችም ከተማችን ተጠቃሚ ሆናለች።”

የባህርዳር ስታዲየም ያለበት የግንባታ ሁኔታ

“ዋናው የእግርኳስ እና አትሌቲክስ ስታዲየም 91 በመቶ ተጠናቋል። የተለያዩ የስፖርት መወዳደሪያ ቦታዎችን ያካተተው አጠቃላይ የስታዲየሙ ስራ ደግሞ 50 በመቶ ላይ ይገኛል። ስታዲየሙ ያለበት ደረጃ ለማድረስ እስካሁን 500 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። ዋናውን ስታዲየም እስከ ቀጣዩ መስከረም ድረስ ለማጠናቀቅ በመስራት ላይ ስንሆን ለፊኒሺንግ ስራም እስከ 300 ሚሊዮን ብር ድረስ ያስፈልገናል።”

ሼህ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲን የሜዳውን ቀሪ ወጪ እሸፍናለሁ ብለዋል?

“ሼህ አልአሙዲ በወልዲያ ዘመናዊ ስታዲየም እየሰሩልን ይገኛሉ። የወልዲያ ስታዲየም ግንባታ ሲጠናቀቅም ለባህርዳር ስታዲየም የጎደለውን አሟላለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል።”

የባህርዳር ስታዲየም የሚጫወት ክለብ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማስገባት ምን እየተሰራ ነው?

“ባለፉት 2 ዓመታት በተከታታይ አንድ ክለብ ወደ ፕሪምየር ሊግ አስገብተናል። ዘንድሮም ያለጥርጥር የምነግራችሁ ተጨማሪ የአማራ ክልል ክለብ ፕሪምየር ሊጉን ይቀላቀላል። ነገርግን በአሁኑ ሰዓት በአማራ ሊግ የሚሳተፉ 38 ክለቦች፣ በብሄራዊ ሊግ 14 ክለቦች፣ እንዲሁም ከ160 በላይ ፕሮጀክቶች በክልላችን አሉ። ይህ ስታዲየም ሲገነባም የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ብቻ እንዲደረግበት ሳይሆን በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ክለቦች እንዲጠቀሙበት ነው።”

በዛሬው ጨዋታ ስለታደመው ህዝብ ብዛት

“የባህርዳር ስታዲየም ሲሰራ በወንበር 50ሺህ፣ ያለወንበር ደግሞ 150ሺህ ህዝብ ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ ነው። ለዛሬው ጨዋታ 68ሺህ ቲኬቶች አዘጋጅተን የነበረ ቢሆንም ቲኬቶቹ ተሽጠው ያለቁት ገና በጊዜ ነበር። ወደሜዳ የመጣው ሰው ከመብዛቱ የተነሳ በርካታ ተመልካቾችን ያለቲኬት አስገብተናል። በኔ ግምት ከ100ሺህ ያላነሰ ህዝብ ዛሬ ስታዲየም በመገኘት ጨዋታውን ተከታትሏል።”

ያጋሩ