የጨዋታ ሪፖርት | ፋሲል ከተማ ከሜዳው ውጪ ድል ማድረጉን ቀጥሏል

በ9ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ጨዋታ በሊጉ ፍፁም የተለያየ አቋም እያሳዩ የሚገኙት ሁለቱ አዲስ አዳጊ ቡድኖችን አገናኝቶ ፋሲል ከተማ በኤዶም ኮድዞ ሁለት ጎሎች አማካይነት ባለሜዳው አዲስ አበባ ከተማን 2-0 ረቷል።

በራሳቸው ሜዳ ላይ የሚጫወቱ እስኪመስል ድረስ በቡድናቸው ዋና መለያ ቀይ እና ነጭ ቀለማት ተውበው በተለይም በካታንጋ በኩል በብዛት በመሆን በዝማሬ ስታድየሙን ሲያሞቁ በነበሩት በፋሲል ከተማ ደጋፊዎች አጀብ ነበር ጨዋታው የጀመረው።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሲጀመር ሁለቱ ቡድኖች በተመጣጠነ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ በሀከለኛው የሜዳ ክፍል ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ በማድረግ ነበር ።

ጨዋታው በዚህ ቀጥሎም በ5ኛው ደቂቃ እንግዶቹ በቀኝ መስመር የሰነዘሩትን ጥቃት ወደ አዲስ አበባዎች የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ይዘው ለመግባት ሲሞክሩ ኳስ በባለሜዳው ቡድን የመሀል ተከላካይ ዲሚጥሮስ ወልደስላሴ በእጅ በመነካቷ የእለቱ አልቢትር የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል። ቡድኑ በጨዋታው መጀመሪያ ያገኘውን ይህን አጋጣሚም ቶጎዋዊው የአፄዎቹ አጥቂ ኤዶም ኮድዞ መቶ ወደግብነት ቀይሮታል ።

ከግቡ መቆጠር በኋላ አዲስ አበባዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ በመሞከር ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክልል እየገቡ ከግቡ ራቅ የሚሉ ሙከራዎችን በሁለቱ አጥቂዎች ኃይሌ እሸቱ እና ኤፍሬም ቀሬ አማካይነት ማድረግ ችለዋል። ነገር ግን ቡድኑ ወደ ፋሲሎች የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ሰብሮ መግባት በኩል በጣም ተቸግሮ ታይቷል።

ፋሲል ከተማዎች በበኩላቸው ከ ኤዶም የፍፁም ቅጣት ምት ጎል በኋላ በሂደት ወደሚታወቁበት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የመጡ ሲሆን በብዛት ወደቀኝ መስመር ባደላ የማጥቃት አጨዋወት የተጋጣሚያቸውን ጎል መፈተሽ ቀጥለዋል። በ32ኛው ደቂቃ ላይም በዚሁ ቀኝ መስመር በኩል በመልሶ ማጥቃት ይዘውት የገቡትን ኳስ ሔኖክ ገምተሳ ሲያሻግርለት ኤዶም ኮድዞ አግኝቶ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አድርጓትል።

ከዚህች ሁለተኛ ግብ ውጪ የአሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ቡድን የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሰዒድ ሃሰን ከመከል ሜዳ አሻምቶት ከነጠረ በኋላ ተክለማርያም ሻንቆ እንደምንም ግብ ከመሆን ያዳነውን ኳስ ጨምሮ በአጥቂ አማካዮቹ በሰለሞን ገብረመድህን እና ኤርሚያስ ሀይሉም ተጨማሪ ሙከራዎችን ማድረግ ችሎ ነበር። ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር የተከላካይ አማካዩን ዘሪሁን ብርሀኑን በቀኝ መስመር ተከላካዩ አማረ በቀለ ቀይሮ የገባው ባለሜዳው ቡድን ጨዋታው በገፋ ቁጥርም ፀጋ አለማየሁን እና ሙሃጅር መኪን የመሳሰሉ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን አማካዮች በማስገባት በመሀል ክፍሉ ላይ ተደጋጋሚ ለውጦችን አድርጓል።

ቡድኑ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ኳስን በመሀል ሜዳ ላይ በመያዝ እና አልፎ አልፎም ከኋላ በሚላኩ ቀትተኛ ኳሶች አጥቂዎችን ለማግኘት ሙከራ ሲያደርግ ተስተውሏል። ያም ሆኖ አዲስ አበባዎች እንደወትሮው ያለቀላቸው የግብ እድሎችን መፍጠር ከብዷቸው አምሽቷል።

ባለሜዳዎቹ ከፊት ባሉት ሁለት አጥቂዎቻቸው እና በአማካዩ ሙሃጅር መኪ እንዲሁም በዲሚጥሮስ ወልደስላሴ አማካይነት የተለያዩ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ውጤቱን መቀየርም ሆነ ማጥበብ ሳይችሉ ቀርተዋል።

የአሰልጣኝ ዘማሪያም ወ/ጊዮርጊስ ቡድን በበኩሉ በሁለተኛው አጋማሽም ተጋጣሚው ኳስ ሲይዝ በተወሰነ መልኩ በማፈግፈግ እና ኳስ በሚነጥቅበትም አጋጣሚ ፈጠን ባለ ከመከላከል ወደማጥቃት በሚደረግ ሽግግር በታታሪ የመሀል አማካዮቹ እና የመስመር አጥቂዎቹ በመታገዝ በተደጋጋሚ ወደተጋጣሚው የመከላከል ወረዳ ለመግባት ችሏል። የቡድኑ አማካዮች እና አጥቂዎች በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተጋጣሚያቸውን ጫና ውስጥ በመክተት እና ኳስ በመንጠቅም የግብ እድሎችን ለመፍጠር ችለዋል። ፋሲሎች ወደግብ አልቀየሯቸውም እንጂ በ ናትናኤል ጋንቹላ እና ሰለሞን ገ/መድህን አማካይነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግም ችለው ነበር። ቡድኑ መሪነቱን ሚያሰፋባቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም ባይችልም በጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ለአዲስ አበባዎች ክፍተት ባለመስጠት የ 2-0 ውጤቱን አስጠብቆ መውጣት ችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የፋሲል ከተማ ተጨዋቾች ሙሉ የጨዋታውን ሰዐት ከፍተኛ ድጋፍ ሲሰጣቸው ለነበረው ደጋፊያቸው ምስጋና አቅርበዋል። ቡድኑም ባስመዘገበው ድል 15 ነጥቦችን በመያዝ ቀድሞ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር አቻ የተለያየውን መከላከያን በግብ ክፍያ በመብለጥ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ተጋጣሚው አዲስ አበባ ከተማ በበኩሉ የተቆጠሩበት ሁለት ግቦች የነበረበትን የግብ እዳ ወደ 6 ከፍ አድርጎ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ለመቀመጥ ተገዷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *