በ9ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን ውሎ የሊጉ ክስተት የሆነው ፋሲል ከተማ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ አዲስ አበባ ከተማን ገጥሞ በቶጎዋዊው ኤዶም ሆሶሮውቪ የመጀመሪያ አጋማሽ 2 ግቦች በመታገዝ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማን 2-0 መርታት ችሏል፡፡
ይህንን ድል ተከትሎ አፄዎቹ ካደረጓቸው ስምንት ጨዋታዎች 15 ነጥቦችን ሰብስበው ከመሪዎቹ ጎራ መቀላቀል ሲችሉ በአንፃሩ ተሸናፊዎቹ አዲስ አበባ ከተማዎች አሁንም በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ – ፋሲል ከተማ
ስለ ጨዋታው
” በፕሪሚየር ሊጉ ላይ የሚገኙ ቡድኖች ከሜዳቸው ውጪ ሲጫወቱ ነጥብ ተጋርቶ መውጣትን ይመርጣሉ፡፡ በአንፃሩ በተቃራኒው በሜዳቸው ሲጫወቱ ማሸነፍን የመፈለግ ነገር አለ፡፡ ነገር ግን እኛ በሜዳችንም ሆነ ከሜዳችን ውጪ ስንጫወት በፕሬሲንግ አጨዋወት አጥቅተን በመጫወት ነጥብ ለማስመዝገብ እየሞከርን እንገኛለን፤ ይህም ይመስለኛል የዛሬውን ጨዋታ አሸንፈን እንድንወጣ ያደረገን፡፡”
“በዛሬው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ አዲስአበባ ከተማዎች ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል ፤ ነገር ግን ከዚህ በፊትም በነበሩ ጨዋታዎች ሲጫወቱ እናዳየናቸው እጅግ በርከት ያሉ ኳሶችን መሀል ሜዳ ላይ ይነካካሉ፡፡ ነገርግን እኛ ጎልን አስቦ በመጫወት የተሻልን ነበርን፡፡ ስለዚህ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተሻለው ቡድን አሸንፏል ማለት ይቻላል፡፡”
የማሸነፍ መንፈስ እና ተነሳሽነት
“የቡድናችን ትልቁ ጥንካሬ የማሸነፍ ስሜታችን ነው፡፡ ይህ ስሜት ደግሞ ከደጋፊዎቻችን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እንደተመለከታችሁት በርካታ ደጋፊ ከጎንደር ድረስ ተጉዞ መጥቷል፡፡ በዚህም የማሸነፍ ስሜታችን ከፍተኛ ነው፡፡”
“አብዛኛዎቹ የቡድኔ ልጆች የተገኙት ከከፍተኛ ሊጉ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ልጆቹ ራሳቸውን ማሳየት ይፈልጋሉ ፤ የቡድኑ አንድነቱ እና መነሳሳቱ ምናልባትም ለውጤት እያበቃን ይገኛል ብዬ አስባለሁ፡፡”
ኤዶም
” ኤዶም በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ግቦችን እያስቆጠረ ይገኛል፡፡ ከእሱ በተጨማሪ ሰለሞን ገብረመድህንም በጣም ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡”
መሻሻል
“ልጆቹ አዕምሮቸው ላይ ስራ ሰርተን ለውጥ ማምጣት ችለናል ፤ ነገርግን ይሄ ደግም የመጨረሻ ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ ከዚህ በላይ መሻሻል ይኖርብናል፡፡”
የሜዳ ጨዋታዎች
“በሜዳችን በሚደረጉ ጨዋታዎች ውጤት ይዘን እየወጣን አይደለም፡፡ በተከታታይ በአቻ ውጤት ነበር ጨዋታዎችን በሜዳችን እየጨረስን የምንገኘው፡፡ ስለዚህም ይሄን በማሻሻል አሁን ባለንበት ደረጃ እንቀጥላለን ብዬ አስባለሁ፡፡”
ህብረት
“የኛ የቡድናችን ኮከቡ ባጠቃላይ ቡድኑ ነው፡፡በህብረት ነው የምንቀሳቀሰው ፤ ቡድኑ ኳስ ይዞም ሆነ ያለ ኳስ ብዙ ይሮጣሉ፡፡ በተለይም በመልሶ ማጥቃት ኳስ ስናገኝ ፊት ላይ ያሉን ልጆች በጣም ፈጣን ናቸው፡፡ ዋናውና ትልቁ ነገር በሜዳችን ስንጫወት ብዙ ቡድኖች መከላከልን መርጠው ስለሚመጡ ብዙ መጫወቻ ክፍተትን አይሰጡንም በዚህም የተነሳ ብዙ ጨዋታዎችን ከሜዳችን ውጪ እያሸንፍን እንገኛለን ምክንያቱም ቡድኖች በሜዳቸው ሲጫወቱ ለማሸነፍ ስለሚጫወቱ በፕሬሲንግ እየተጫወትን ነጥቦችን መያዝ ችለናል፡፡”
ደጋፊዎች
” የቡድናችን ትልቁ ሀይል ደጋፊዎቻችን ናቸው፤ በዛሬው ጨዋታ ከቡድኑም በላይ ጥሩ ለነበሩት ደጋፊዎቻችን 3 ነጥብ ይገባቸዋል፤ በዚህ አጋጣሚ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እፈልጋለሁ፡፡”
ስዩም ከበደ – አዲስ አበባ ከተማ
ስለ ጨዋታው
“በዛሬው እለት የነበረው የተጫዋቾቼ እንቅስቃሴ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተለየ ነበር፡፡ ጥሩ ነው ለማለት አያስችልም ፤ በተለይም ግብ ባስተናገድን ቁጥር ያለመረጋጋት ይታያል፡፡ ይህም ደግሞ በልምድ የሚመጣ ይመስለኛል፡፡ በጥቅሉ አልፎ አልፎ ብልጭ ድርግም ከሚለው እንቅስቃሴያችን በስተቀር ልክ እንደዚህ ቀደሙ ስንሸነፍ እንደምናደርገው ኳስን ተቆጣጥረን በአጨራረስ ችግሮች ሳይሆን በበርካታ መመዘኛዎች ልክ ያልነበርንበት ጨዋታ ስለነበር ሽንፈቱን የምንቀበለው ነው፡፡”
መሻሻል
“ችግር ላይ እንገኛለን፡፡ ይህንንም ለማስተካከል ጥረት እናደርጋለን፡፡”
“ዝግጅታችንን ዘግይተን እንደመጀመራችን እንደ ሌሎች ቡድኖች የምንፈልጋቸውን ተጫዋቾች ማግኘት አልቻልንም፤ ይህንንም በሁለተኛው ዙር ለመቅረፍ ከ6 ያላነሱ ተጫዋቾች ከጋና እና ካሜሮን ለማስመጣት ሂደት ላይ እንገኛለን ያም ቢሆን ግን እስከዛው ድረስ ባሉን ልጆች እያስተካከልን መሄድ ነው፡፡”
ጉዳት
“በመሀል ተከላካይ ስፍራ ላይ በቋሚነት የምንጠቀምባቸው ሶስት ተጨዋቾች ጉዳት ላይ ይገኛሉ፡፡”