የጨዋታ ሪፖርት | የአላዛር የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ለወላይታ ድቻ 1 ነጥብ አስገኝታለች

Read Time:2 Minute, 0 Second

በ9ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የደቡብ ደርቢ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ 3-3 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

የሀዋሳ ከተማ ስታዲየም ገና ጨዋታው ሳይጀመር በደጋፊዎች ድባብ እና ህብረ  ዝማሬ የደመቀ ሲሆን በበርካታ ተመልካቾች ታጅቦ የተካሄደው ጨዋታ ጥሩ የኳስ ፍሰት የታየበት እና አዝናኝ ሆኖ አልፏል፡፡

በመጀመሪያወቹ 15 ደቂቃዎች ሀዋሳ ከተማ የተሻለ የእነንቅስቃሴ የበላይነት ቢኖረውም ወላይታ ድቻወች በተሻጋሪ ኳሶች ተሽለው ታይተዋል፡፡

በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ቶጎዊው አጥቂ አራፋት ጃኮ ከግብ ጠባቂው ወንደሰን ገረመው ጋር አንድ ለአንድ በመገናኘት ተደጋጋሚ ኳሶችን አምክኗል፡፡ በአንፃሩ በተሻጋሪ ኳሶች ሲጠቀሙ የነበሩት ድቻወች በ24ኛው ደቂቃ ላይ በመስመር ፈጣን እንቅስቃሴን  ሲያደርግ የነበረው ፀጋዬ ብርሀኑ መሬት ለመሬት አክርሮ የመታትን ኳስ የሀዋሳ ከተማ ተከላካይ መላኩ ወልዴ ለማውጣት ሲሞክር ተጨርፋ በሀዋሳ መረብ ላይ አርፋለች፡፡

ከግቡ በኋላ ወላይታ ድቻዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር  ጫና ፈጥረው ተጫውተዋል፡፡ በተለይም የቀኝ መስመር ተጫዋቹ ፀጋዬ ብርሀኑ ተደጋጋሚ አደጋ የሚፈጥሩ ኳሶችን ከመስመር በማድረስ ድንቅ ነበር፡፡ በ28ኛው ደቂቃም ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አሻግሮ ተከላካዩ ቶማስ ስምረቱ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ የድቻን መሪነት ወደ ሁለት አደርጓል፡፡

ሀዋሳ ከተማዎች 2-0 ከመመራት ተነስተው አቻ ለመሆን ብዙም አልተቸገሩም፡፡ በ33ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ያሻገረውን ኳስ ኃይማኖት ሲጨርፈው ቶጎዊው አራፋት ጃኮ ሀዋሳ ወደ ጨዋታው የተመለሰበትን ግብ አስቆጥሯል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃ ሲቀር ደግሞ ጃኮ አረፋት ያቀበለውን ኳስ ፍሬው ሰለምን አስቆጥሮ ሀዋሳን አቻ በማድረግ ወደ መልበሻ አቅንተዋል፡፡

ማራኪ የኳስ ፍሰት በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል፡፡

በ56ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ዘካርያስ ከፍሬው የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ሳጥኑ ሲገባ በሙባረክ ሽኩር በመጠለፉ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ፍሬው መትቶ ሀዋሳን መሪ ማድረግ ቻለ፡፡

ሀዋሳዎች ከግቡ መቆጠር በኋላም ጫና ፈጥረው በመጫወት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ቢምክሩም የወላይታ ድቻን የተከላካይ መስመር መስበር አልቻሉም፡፡ በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም አቻ የሚያደርጋቸውን ግብ ለማግኘት ሲጥሱ ተስተውሏል፡፡

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በዛብህ መለዮ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ አላዛር ፋሲካ  የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ወላይታ ድቻ ወርቃማ 1 ነጥብ ይዞ እንዲወጣ አድርጎታል፡፡ ሀዋሳ ከተማ በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ድቻን ለማሸነፍ ቢቃረብም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

መሣይ ተፈሪ – ወላይታ ድቻ

“በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ የሀዋሳ አጨዋወት ደስ የሚል ነበር፡፡ እኛም ብዙ ጥረት አድርገናል ፤ ልጆቼ ምን ያህል ግብ ለማስቆጠር ያላቸውን ፍላጎት አይቻለው፡፡

ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ

“ጠንካራ ጨዋታ ነበር፡፡ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ችለናል፡፡ ሆኖም መጠነኛ ክፍተቶች ነበሩብን፡፡ አሁን ባለን ስብስብ ሶስት ግብ ማስቆጠር ጥሩ ነው፡፡ ከታች ባደጉ ተጫዋቾች ነው የምንጠቀመው፡፡”

” ነጥብ ተጋርተን በመውጣታችን ቅር ብሎኛል፡፡ እኛ ከነሱ የታሻልን ነበርን፡፡ ግብ ተቆጥሮብን ማስቆጠራችን ጥሩ ጎናችን ነው፡፡”

” አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች በጉዳት አልነበሩም፡፡ ግብ ጠባቂያችን ዛሬ የመጀመሪያ ጫወታው ነው ፤ ተጫዋቾቼ ቢጎዱም ወጣቶቹ ባሳዩን ጥሩ እንቅስቃሴ ረክቻለው፡፡”

” ገና ብዙ ጨዋታ ስለሚቀረን ስጋት የለብንም ፡፡ “

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
ያጋሩ

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

Leave a Reply

error: Content is protected !!