የጨዋታ ሪፖርት | አዳማ የሊጉን መሪነት ሊጨብጥበት የሚችልበትን ወርቃማ እድል አምክኗል

9ኛ ሳምንቱን በያዘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ 9፡00 በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአናት የተቀመጠው ኤሌክትሪክን አስተናግዶ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡ አዳማዎች ሊጉን የሚመሩበትን እድል በመጨረሻ ሰአት ባባከኑት የፍፁም ቅጣት ምት ምክንያት ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ወደ መስመር ባደላ መልኩ በረጃጅሙ በሚጣሉ ኳሶች የግብ እድልን ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል፡፡ የጨዋታውም የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራም በ9ኛው ደቂቃ ፋሲካ አስፋው ከመሀል በረጅሙ የላከለትን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በግሩም ሆኔታ ከተቆጣጠረ በኃላ ወደ ግብ ቢሞክርም የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ሱሌይማን አቡ በጥሩ ሆኔታ አድኖበታል፡፡ በ20ኛው ደቂቃ ብሩክ ቃልቦሬ ያሻማውን የማዕዘን ምት አዲስ ህንፃ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ ከታዩት የግብ ሙከራዎች የምትጠቀስ ነበረች፡፡

በተመሳሳይ በቀጥተኛ አጨዋወት በ24ኛው ደቂቃ ጉዳት ላይ የሚገኘውን አምበላቸውን ሱሌይማን መሀመድን ተክቶ የግራ ተከላካይ ስፍራ ላይ የተሰለፈው ሲሳይ ቶሊ ያሻማውን ኳስ ዳዋ ሆቴሳ ሚዛኑን ስቶ ወድቆ ሳይጠቀምባት ቀርቷል፡፡ 

በአንጻሩ እጅግ በርከት ያሉ ኳሶችን መሀል ሜዳ ላይ በአጭር ቅብብል ሲነካኩ የነበሩት ኤለክትሪኮች ይህ ነው የሚባል የግብ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በተቀዛቀዘው የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ካገኛቸው የግብ እድሎች መካከል በ25ኛው ደቂቃ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን ኳስ ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ኢብራሂም ፎፋኖ ከቀኝ መስመር ወደ አዳማ የግብ ክልል አመቻችቶ አቀብሎት ፍፁም ገብረማርያም የሳታት ኳስ

የምታስቆጭ ነበረች፡፡ በ33ኛው ደቂቃ ላይ ኤሌክትሪኮች ያገኙትን የማእዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ሙሉዓለም የሳተው ኳስ ሌላኛው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በበርካታ መመዘኛዎች ከመጀመሪያው ተዳክመው ተስተውለዋል፡፡ በዚሁ አሰልቺ በነበረው የሁለተኛ አጋማሽ ይህ ነው የሚባል የግብ አጋጣሚ ለማየት እስከ 67ኛው ደቂቃ መጠበቅ ግድ ብሏል፡፡

በ67ኛው ደቂቃ የአዳማው ግብጠባቂ ጃኮብ ፔንዜ በቀጥታ የመታውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም የኤሌክትሪክ ተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ የግል ጥረቱን በመጠቀም ወደ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል ከገባ በኃላ የሞከራት ኳስ በሱይይማን አቦ ጥረት ግብ ከመሆን ድናለች፡፡ 

በ72ኛው ደቂቃ ኤሌክትሪኮች በአዳማ ቀኝ የግብ ክልል አካባቢ ያገኙትን ቅጣት ምት ዳዊት እስጢፋኖስ በቀጥታ መትቶ የአዳማው ግብጠባቂ ጃኮብ ፔንዜ ሲመልስ በቅርብ ርቀት የነበረው ሙሉዓለም ጥላሁን ገጭቶ ቢያስቆጥርም ዳኛው ከጨዋታ ውጪ በሚል ሳያፀድቁት ቀርተዋል፡፡

ከዚህ በኃላ እንግዳዎቹ አዳማ ከተማዎች በቀጥታ ከበረኛቸው እንዲሁም ከተከላካዮች በሚጣሉ ኳሶች ለማጥቃት ሲሞክሩ በአንጻሩ ባለሜዳዎቹ ኤሌክትሪኮች ከቋሙ ኳሶች እንዲሁም ከዳዊት እስጢፋኖስ ላይ መሠረት አድርገው ከሱ እግር በሚነሱ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡

ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ ተብሎ በሚጠበቅበት ሰአት በ93ኛው ደቂቃ ላይ የኤሌክትሪኩ የቀኝ መስመር ተከላካይ አወት ገብረሚካኤል ተቀይሮ በገባው ቡልቻ ሹራ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሙጂብ ቃሲም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ አዳማ 3 ነጥብ ይዞ የሚወጣበትን ወርቃማ እድልም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ ካደረጋቸው 9 ጨዋታዎች 18 ነጥቦችን ሰብስቦ አሁንም ከመሪዎቹ ጎራ ሲገኝ በአንጻሩ ኤሌክትሪኮች በዘንድሮው የውድድር ዘመን ካደረጓቸው 9 ጨዋታዎች ምንም ማሸነፍ ሳይችሉ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ፡፡

Leave a Reply