ኢትዮ ኤሌክትሪክ 0-0 አዳማ ከተማ | የአሰልጣኞች አስተያየት

አሸናፊ በቀለ – አዳማ ከተማ

ስለ ጨዋታው

“ያጋጠመንን ዕድል አልተጠቀምንበትም፡፡ ኳስን ከነስህተቱ መቀበል ነው ፤ ተቀብለነዋል፡፡”

“የዛሬው ቡድኔ እንደጠበቅኩት አይደለም፤ የኳስ ፍሰቱ ጥሩ አልነበረም፡፡ ጨዋታው የሃይል አጨዋወት የበዛበት ነበር ፤ ለተመልካች ማራኪ የሆነ እግርኳስ በሁለታችንም በኩል አልነበረም፡፡ የተገኙ የግብ አጋጣሚዎችንም መጠቀም አልቻልንም፡፡ እነዚህ ለወደፊቱ የምናርማቸው ነገሮች ናቸው፡፡”

ቡድኑ ውስጥ ስላለው መንፈስ

“ብናሸንፍ የበለጠ ተነሳሽነቱ ይጨምር ነበር፡፡ አሁንም እዚያው መሪዎቹ ጎራ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ይህም ቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ትኩረት እንድናደርግ እና ካለን ነገር የበለጠ እንድንሰራ ያደርገናል፡፡”

ከሜዳ ውጪ ስለመጫወት

“አዲስ አበባ ስታዲየም የእኔ ሜዳ ነው፤ የሌላ ሜዳ ነው የምትለው አይደለም፡፡ የትኛውም ሜዳ የኢትዮጵያ ሜዳ ነው፡፡  ልዩነቱ የደጋፊ መኖር አለመኖር ካልሆነ በስተቀር የተሻለ አቅም ያለው ቡድን ሁልጊዜ ያሸንፋል፡፡ ዋናው ነገር ይኼ ነው እንጂ እኛ የትም ሄደን ብንጫወት የሚፈጥርብን ተፅዕኖ የለም፡፡”

ብርሃኑ ባዩ – ኤሌክትሪክ

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው በሁለታችንም በኩል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር፡፡ በተለይ በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ሁለታችንም ለጎል የቀረቡ አጋጣሚዎችን ስተናል፡፡ በጨዋታው የታየው እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር፡፡ የነበረው የመጫወት ፍላጎትም ጥሩ ነው፡፡”

“መጨረሻ ላይ እነሱ ያገኙት ፍፁም ቅጣት ምት ለኛ ተስፋ አስቆራጭ ነበረ፡፡ ነገርግን ያው የተመታው ኳስ ከግቡ ውጪ ሆኗል፡፡”

ቡድኑ ላይ ስላለው ጫና

“በተጫዋቾቻችን ላይ በተለይም አጥቂዎቻችን ላይ ጫና መኖሩ ግልፅ ነው፡፡  ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል እንደውም ካሉት ክለቦች የተሻልን ነን ማለት ይቻላል፡፡ ኳስ እና መረብን የማገናኘቱ ችግር ዛሬም በአጥቂዎቻችን ላይ መታየቱ ይህን የስነልቦና ጫና የሚያሳየን ነው፡፡”

ቡድኑ ስላለበት ችግር

“ውጤትን ይዞ መውጣት ያለመቻል ባለፈው ዓመትም የነበረብን ችግር ነው፡፡ ባለፉት አራት ጨዋታዎች እየመራን ቆይተን በግል በሚሰሩ ስህተቶች ውጤት እያጣን እንወጣ ነበር፡፡ በፕሪሲዝን ወቅት ይህንን ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶች ነበሩ፡፡ ነገርግን ክለቡን በበላይነት የሚመራው አካል ሽግግር ላይ ስለነበረ ለማስፈረም የመረጥናቸው ልጆች በወቅቱ ማግኘት ባለመቻላችን ወደተለያዩ ክለቦች ገብተዋል፡፡ አምና የነበረው ክፍተት እስካሁንም አለ፡፡”

“ባሉት ተጫዋቾች የመጀመሪያውን ዙር እንደምንም ለመውጣት እንሞክራለን፡፡ እነዚህን ክፍተቶች በእርግጠኛነት በሁለተኛው ዙር ለመድፈን ጥረቶች ከወዲሁ ጀምረናል፡፡ ጥሩ ተጫዋቾችን በየቦታው ለማግኘት እየሞከርን ነው፡፡ በሁለተኛው ዙር ላይ ጥሩ መሻሻል እናሳያለን ብዬ አስባለሁ፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *