በ9ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ በቀላሉ 3-0 በማሸነፍ መሪዎቹን ተጠግቷል፡፡
ፈረሰኞቹ ባሳለፍነው እሁድ በሸገር ደርቢ በኢትዮጵያ ቡና 1-0 ከተሸነፈው ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ከሀገሩ ዮጋንዳ ጋር በዱባይ የሚገኘው ሮበርት ኦዶንካራን በፍሬው ጌትነት ፣ ተከላካይ መስመር ላይ ምንተስኖት አዳነን ወደ ቀድሞው የአማካይ ተከላካይነት ሚናው መልሰው በምትኩ ደጉ ደበበን ከሳልሀዲን ባርጌቾ ጋር ሲያጣምሩት በአማካይ ስፍራ ላይ ያስር ሙጌርዋን አስወጥተው ዘካሪያስ ቱጂን እንዲሁም ፊት ላይ ራምኬል ሎክን በአዳነ ግርማ ተክተው በ4-2-3-1 በሚመስል ቅርፅ ወደ ጨዋታው ሲገቡ በአንጻሩ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ባልተለመደ መልኩ በሜዳው በአርባምንጭ ከተማ ከተሸነፈው ቡድን በተመሳሳይ 4-4-2 ቅርፅ መጠነኛ ለውጦችን መሀል ክፍላቸው ላይ አድርገው ነበር፡፡
የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ድሬዳዎች በፈጣን ከመላከል ወደ ማጥቃት በተደረጉ ሽግግሮች በተገኙ ኳሶች ሀብታሙ ወልዴ እና ዘላለም ኢሳያስ አግኝተው ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡
በ10ኛው ደቂቃ ላይ ዘካርያስ ቱጂ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ሰልሀዲን ቢሞክርም ኳሱ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል፡፡ በተመሳሳይ በ15ኛው ደቂቃ ላይ ሰልሀዲን ሰኢድ ከአዳነ ግርማ የተሻገረለትን ኳስ በፍጥነት ወደ እሱ እየመጣ ከነበረው የድሬዳዋው ግብጠባቂ ሳምሶን አሰፋ በላይ ከፍ አድርጎ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
በመጀመሪያው 15 ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአመዛኙ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ቢኖራቸውም የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው የሚታወቁበት የጥብቅ መከላከል የሚፈልጉትን ከማድረግ አግዷቸዋል፡፡
በ22ኛው ደቂቃ ሄኖክ አዱኛ ወደ ኃላ ለግብ ጠባቂው ሳምሶን አሰፋ የመለሰለትን ኳስ ሳምሶን አሰፋ ስህተት በመስራቱ የተገኘችውን ኳስ ምንተስኖት አዳነ አግኝቶ ቢሞክርም ኳሷ ኢማዋን ሳትጠብቅ ቀርታለች፡፡ በተመሳሳይ በ26ኛው ደቂቃ ላይ ዘካሪያስ ቱጂ ከግራ ያሻማውን ኳስ ምንተስኖት ገጭቶ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት ኳስ የምታስቆጭ ነበረች፡፡
በ30ኛው ደቂቃ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከድሬዳዋ የግብ ክልል 25 ሜትር አካባቢ ያገኙትን ቀጣት ምት አበባው ቡጣቆ በግሩም ሆኔታ መትቶ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ሲመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው አዳነ ግርማ በግንባር በመግጨት ፈረሰኞቹን ቀዳሚ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል፡፡
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ እስከ ግቧ መቆጠር ድረስ በጥብቅ መከላከል ማለትም ቡድኑ ኳስ በሚያጣ ጊዜ ሁሉም ተጫዋቾች ለማለት በሚያስደፍር ሆኔታ በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ አፈግፍገው ሲከላከሉ ቢቆዩም ከግቧ መቆጠር በኃላ በመጠኑም ቢሆን አጨዋወታቸውን በመቀየር በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በተሻለ የተጫዋች ቁጥራቸውን ወደ ፊት ሲሄዱ በማብዛት ለመንቀሳቀስ ጥረት አድርገዋል፤ ምንም እንኳን እንቅስቃሴያቸው በቀኝ መስመር ባላቸው ተሰላፊዎች ማለትም በመስመር ተከላካዮ ሄኖክ አዱኛ እና የመስመር አማካዩ ሱራፌል ዳንኤል በኩል ያጋደለ ቢመስልም፡፡
ጊዮርጊሶች በ42ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻማው ኳስ ምንተስኖት ሞክሮ ኢላማዋን ሳትጠብቅ ከቀረችው ኳስ በተጨማሪም በርከት ያሉ ኳሶችን በመስመር ላይ ከሚገኙት አቡበከር ሳኒ እና ዘካሪያስ ቱጂ ወደ መሀል በቀጥታ በማሻማት ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም የድሬዳዋ ተከላካዮች ያንን ከማድረግ አግደዋቸዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ አሰልጣኝ ማርት ኖይ በመጀመሪያው አጋማሽ ከምንተስኖት አዳነ ጋር ተጋጭቶ አፍንጫው ላይ ጉዳት የደረሰበት ሰልሀዲን በርጊቾን በወጣቱ ፍሬዘር ካሣ መተካት ችለዋል፡፡ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ አማካዩ ዘላለም ኢሳያስን አስወጥተው ይሁን እንደሻውን በእረፍት ሰአት ቀይረው አስገብተዋል፡፡
በ50ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ የጊዮርጊስ ተከላካዮች ሲመልሱ ያገኘውን ኳስ እንደመጣ በቮሊ ቢሞክርም ፍሬው ብርሃኑ ሊያድንበት ችሏል፡፡
በአንጻሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ53ኛው ደቂቃ ላይ ሰልሀዲን ሰኢድ በግራ መስመር ሄኖክ አዱኛን አልፎ በቀጥታ ወደ ግብ የሞከራትን ኳስ የድሬ ተከላካዮች ተደርበውበት የተገኘችውን ኳስ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያመሸው ምንተስኖት አዳነ ሞክሮ ከግቡ አናት በላይ የላካት ሙከራ ተጠቃሽ ነበረች፡፡
በ67ኛው ደቂቃ ላይ ሰልሀዲን ሰኢድ በቀጥታ ከተከላካዮች የተላከለትን ኳስ ከሁለቱ የድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮች ጋር ታግሎ አልፎ በግሩም ሆኔታ የመታት ኳስ ከመረብ ተዋህዳ የፈረሰኞቹን መሪነት 2-0 ያሳደገችዋን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ ሁለተኛዋን ግብ ያስቆጠረው ሰልሀዲን ሰኢድ ከድሬዳዋ የግብ ክልል በግምት 20ሜትር አካባቢ የተገኘችውን የቅጣት ምት በቀጥታ መቶ ለጥቂት የወጣችበት ኳስ ሌላኛዋ በፈረሰኞቹ በኩል የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡
ከግቧ መቆጠር በኃላ ድሬዳዋዎች የመስመር ተጫዋቹን ረመዳን ነስሮን አስወጥተው አጥቂውን ፋአድ ኢብራሂምን በማስገባት ውጤቱን ለመቀልበስ ጥረት አድርገዋል፡፡ በአንጻሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በ76ኛው እና በ78ኛው ደቂቃ ላይ አዳነ ግርማን እና ዘካሪያስ ቱጂን አስወጥተው ራምኪሎክ እና ምንያህል ተሾመን በማስገባት ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል፡፡
በ83ኛው ደቂቃ ቡርኪናፋሶዋዊው አብዱልከሪም ኒኪማ ከሰልሀዲን ሰኢድ የተላከትን ኳስ ተቆጣጥሮ በሚያምር አጨራረስ የክለቡን ሶስተኛ ግብ ሊያስቆጥር ችሏል፡፡
በዚሁ በሁለተኛው አጋማሽ ፈረሰኞቹ ኳስ መስርቶ በመጫወትም ሆነ ወደ ግብ በመድረስ ከተጋጣሚያቸው ተሽለው ተስተውሏል በአንጻሩ በድሬዳዋ ከተማ በኩል የቀኝ መስመር ተከላካዮ ሄኖክ አዱኛ እና ተቀይሮ የገባው ይሁን እንደሻው ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ ፈረሰኞቹ ከመሪዎቹ ያላቸውን ልዩነት በማጥበብ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በመጨረሻ ካደረጓቸው ያለፉት 4 ጨዋታዎች በሶስቱ ተሸንፈው አስከፊ ጊዜን እያሳለፉ ይገኛል፡፡