የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የህክምና ኮሚቴ ለ4 ወራት ያህል ሲያካሂደው የነበረውን የ17 እና 20 ዓመት በታች ተጫዋቾች እድሜ ማረጋገጫ ምርመራ ውጤት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በትናንትናው ዕለት በኢንተርኮንቲነንታል አዲስ ሆቴል መግለጫ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የህክምና ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር ነስረዲን አብዱላሂ ባሰሙት የመክፈቻ ንግግር በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የሚታየውን የተተኪ ችግር ለመፍታት ፌዴሬሽኑ በተለያዩ የእድሜ እርከኖች ላይ ውድድሮችን አዘጋጅቶ እያካሄደ መሆኑን አስታውሰው በዚህ ላይ የስፖርት ህክምና ኮሚቴው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ዶ/ር ነስረዲን አምና የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው ለነበረው ጨዋታ ተጨዋቾች ሲመረጡ ከ17 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ከሚጫወቱ 87 ተጫዋቾች የMRI ምርመራ አድርገው 9ኙ ብቻ ማለፋቸው፤ ከዚያም ከሊጉ ውጪ ያሉ ከ200 በላይ ታዳጊ ወጣቶች ምርመራ ተደርጎላቸው 27ቱ የመጨረሻው ምርጫ አልፈው በብሔራዊ ቡድኑ የተካተቱበት ሂደት ፌዴሬሽኑን ያስደነገጠ እና አሰራሩንም እንዲፈትሽ ያደረገው እንደነበረ ገልፀዋል።
በመቀጠል ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ በበኩላቸው ፌዴሬሽኑ ባስቀመጠው የ5 ዓመት ስትራቴጂ መሠረት የውስጥ አሰራሩን እያስተካከለ መምጣቱን ጠቁመው በተጫዋቾች ዕድሜ ተገቢነት ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሰራው ያለው ስራም የዚህ አካል መሆኑን አስታውቀዋል። አቶ ጁነይዲ አክለውም “የኢትዮጵያ እግርኳስ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው ትክክለኛ እድሜ ያላቸው ወጣቶችን ማብቃት ስንችል ነው፤” ሲሉ አመራሩ ይህን ችግር ለመቅረፍ ቁርጠኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ እና አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድኖችን ለረጅም ዓመታት በዋና ሐኪምነት ያገለገሉት ዶ/ር አያሌው ጥላሁን እስከዛሬ የዕድሜ ገደብ ያለፋቸውን ተጫዋቾች በቡድን ውስጥ ለማካተት የፊት ገፅታን ከመቀየር እስከ ፓስፖርት ማስለወጥ ድረስ ብዙ የተበላሸ አሠራር ሲሰራ እንደነበር አጋልጠው ይህም የእግርኳሱን ዕድገት ማቀጨጩን አምነዋል።
12 የሚሆኑ ከፍተኛ የጤና ባለሞያዎች ተሳታፊ በነበሩበት ምርመራ 2010 የሚሆኑ ወጣቶች ተመርምረው 982 ተጫዋቾች በአካላዊ ምርመራ፣ እንዲሁም 326 ልጆች በMRI ምርመራ ሲወድቁ ቀሪዎቹ 702 ተጫዋቾች አልፈው ውድድሮቹ ላይ ለመሳተፍ ፈቃድ አግኝተዋል። በጋዜጣዊ መግለጫው የህክምና ባለሞያዎቹ የMRI ቴክኖሎጂ እንዴት የተጫዋቾቹን ዕድሜ ማወቅ እንደሚያስችል በተወሰነ ደረጃ በምስል ለማሳየት ሞክረዋል።
ፌዴሬሽኑ ቀድሞ የነበረውን የወጣት ተጫዋቾች ምዝገባ ዘዴ በኮምፒዩተር በተደገፈ መልኩ እንደቀየረም የተነገረ ሲሆን ይህም ከተለያዩ ክለቦች ጋር በመምጣት ምርመራውን በተደጋጋሚ ወስደው ለማታለል የሚሞክሩ ተጫዋቾችን ለመለየት እንዳስቻለ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ የMRI ምርመራውን ሌላ ሰው እንዲያደርግላቸው ማድረግን ጨምሮ ሌሎች የማታለል ሙከራዎች ቢደረጉም በተዘረጋው አሠራር ምክኒያት አለመሳካቱንና የምርመራ ሂደቱንም በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ እንደተቻለ ተነግሯል።
ዶ/ር አያሌው በመጨረሻም በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ የስፖርት ህክምናው የተሰጠው ዝቅተኛ ቦታን በሃገራችን ካሉ 154 ቡድኖች 84% የሚሆኑት የህክምና ባለሙያ የሌላቸው መሆኑን ዋቢ በማድረግ ተናግረዋል። በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከአንዱ ክለብ ወደሌላው ከተዘዋወሩ ተጫዋቾች ውስጥ እስከ 60% ድረስ የሚሆኑት የጉልበት ወይም የብሽሽት ጉዳት እንደነበረባቸው ገልፀው ክለቦች ከዝውውር በፊት ተጫዋቾች የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ በማስገደድ እና ለስፖርት ህክምናውም ተገቢውን ቦታ በመስጠት ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የህክምና ኮሚቴው ይህንን ምርመራ በሴቶች እግርኳስ ላይ በቅርቡ ለመጀመር እና የጨዋታ ዳኞችና ኮሚሽነሮችም በተለይ በአይን ላይ ያተኮረ የህክምና ምርመራ እንዲያደርጉ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።