በአፍሪካ እግርኳስ ድንቅ ብቃታቸውን ላሳዩ ተጫዋቾች እና በእግርኳሱ ጥሩ የሰሩ ሰዎችን የሚሸልመው የግሎ ካፍ አመታዊ ሽልማት ሐሙስ ምሽት አቡጃ ናይጄሪያ ላይ ተደርጓል፡፡ እንደተጠበቀው አልጄሪያዊው ሪያድ ማህሬዝ የአመቱ ምርጥ የአፍሪካ ተጫዋች ሲሰኝ ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ዴኒስ ኦኒያንጎ በአፍሪካ ውስጥ የሚጫወት የአፍሪካ ምርጥ ተብሏል፡፡
በናይጄሪያው የቴሌኮሚኒኬሽን ድርጅት ግሎ ስም ስፖንሰር በተደረገው የሽልማት ስነ-ስርዓት በግብፅ ሚዲያዎች በሙስና ወንጀል በሳምንቱ የተብጠለጠሉት የካፍ ፕሬዝደንት ኢሳ ሃያቱ ተገኝተዋል፡፡
ሪያድ ማህሬዝ የዐመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ተጫዋች የተባለ የመጀመሪያው ሰሜን አፍሪካዊ መሆን ችሏል፡፡ በእንግሊዙ ሌስተር ሲቲ የእግርኳስ ህይወቱን የሚመራው ማህሬዝ ጋቦናዊውን ፒየር ኤምሪክ ኦባሚያንግ እና ሴኔጋላዊውን ሳዲዮ ማኔን አስከትሎ ነው ክብሩን የተዳጀው፡፡ በበረሃ ቀበሮዎቹን እና በሌስተር ሲቲ ጥሩ እንቅስቃሴ በውድድር ዘመኑ ያሳየው ማህሬዝ 361 ድምፆችን ሲያገኝ ኦባሚያንግ እና ማኔ 313 እና 186 ድምፆችን በማግኘት ተከትለውታል፡፡
በአፍሪካ የሚጫወት የአመቱ ምርጥ የአፍሪካ ተጫዋች ሽልማት ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ግብ ጠባቂ አምርቷል፡፡ ሃገሩ ዩጋንዳ ከ39 ዓመት በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ስታልፍ ቁልፍ ሚና የነበረው ከ1997-1998 ለቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫወተው ዴኒስ ኦኒያንጎ በ252 ድምፅ የአመቱ ምርጥ ተብሏል፡፡ ኦኒያንጎ ከደቡብ አፍሪካው ክለቡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ ነበር፡፡ ኦኒያንጎን ተከትለው የዚምባቡዌው ካማ ቢሊያት እና የዛምቢያው ሬንፎርድ ካላባ በ228 እና 206 ድምፅ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነዋል፡፡
የአመቱ ምርጥ ሴት ተጫዋች ናይጄሪያዋ ግብ አዳኝ አሲሳት ኦሾአላ ተብላለች፡፡ ሃገሯ ናይጄሪያ የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ክብርን ዳግም እንድታገኝ ያደረገችው የፊት መስመር ተሰላፊዋ ሽልማቱን ስታሳካ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም፡፡
ደቡብ አፍሪካዊው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ አሰልጣኝ ፒትሶ ሞሴሜኒ የአመቱ የአፍሪካ ምርጥ አሰልጣኝ ተብሏል፡፡ ሰርቢያዊው የዩጋንዳ አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን ሚቾ ከዕጮዎቹ ውስጥ መካከል ነበር፡፡ ሚቾ የአመቱ ምርጥ አሰልጣኝነት ክብርን ባያገኝም እሱ የሚያሰለጥናት ዩጋንዳ የአመቱ ምርጥ ብሄራዊ ቡድን ተብላለች፡፡ ከ39 ዓመት በኃላ ክሬንሶቹ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ሲመለሱ የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ላይ ባደረጉዋቸው ሁለት ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርባቸው ወጥተዋል፡፡ ምርጥ የአፍሪካ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የሪከርድ የአፍሪካ ቻምፒዮኗ ናይጄሪያ ሆናለች፡፡
የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የአመቱ ምርጥ ክለብ ተብሏል፡፡ ዓምና ክብሩን ያሳከው የዲ.ሪ. ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ ነበር፡፡ የአምቱ ምርጥ ዳኛ አሁንም ዳግም ወደ ጋምቢያዊው ባካሪ ፓፓ ጋሳማ አምርቷል፡፡
ሱዳን በ1970 ባስተናገደችው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ላይ አምስት ግቦችን ያሳረፈው የኮትዲቯሩ ሉረን ፖኩ እና የካሜሮኑ ኢሚሊየን ማባንጎ በካፍ ልዩ ሽልማት ተብርክቶላቸውል፡፡ ፓኩ ባሳለፍነው ህዳር ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው፡፡
በሽልማቱ ድምፅ የሰጡት የብሄራዊ ቡድኖች አሰልጣኝ ወይም የቴክኒክ ዳይሬክተሮች፣ የካፍ ሚዲያ ኮሚቴ አባላት፣ የካፍ የቴክኒክ እና ልማት ኮሚቴ አባላት እና 20 የሚሆኑ የኤክስፐርቶች ፓናል ነው፡፡
የአሸናፊዎች ዝርዝር
አፍሪካ ምርጥ ተጫዋች
ሪያድ ማህሬዝ (አልጄሪያ እና ሌስተር ሲቲ)
ፒየር ኤምሪክ ኦባሚያንግ (ጋቦን እና ቦሪሲያ ዶርቱሙንድ)
ሳድዮ ማኔ (ሰኔጋል እና ሊቨርፑል)
በአፍሪካ የሚጫወት የአመቱ ምርጥ አፍሪካ ተጫዋች
ዴኒስ ኦኒያንጎ (ዩጋንዳ እና ማሜሎዲ ሰንዳውንስ)
ካማ ቢሊያት (ዚምባቡዌ እና ማሌሎዲ ሰንዳውንስ)
ሬንፎርድ ካላባ (ዛምቢያ እና ቲፒ ማዜምቤ)
የአፍሪካ ምርጥ ሴት ተጫዋች
አሲሳት ኦሾአላ (ናይጄሪያ እና የአርሰናል ሴቶች ቡድን)
የአመቱ ተስፋሰጪ ተጫዋች
ኬሌቺ ኢያናቾ (ናይጄሪያ እና ማንችስተር ሲቲ)
የአመቱ ምርጥ ወጣት ተጫዋች
አሌክስ ኢዮቢ (ናይጄሪያ እና አርሰናል)
የአመቱ ምርጥ አሰልጣኝ
ፒትሶ ሞሴሜኔ (ደቡብ አፍሪካ እና ማሜሎዲ ሰንዳውንስ)
የአመቱ ምርጥ ክለብ
ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ)
የአመቱ ምርጥ ብሄራዊ ቡድን
ዩጋንዳ (በወንዶች) እና ናይጄሪያ (በሴቶች)
የአመቱ ምርጥ ዳኛ
ባካሪ ፓፓ ጋሳማ (ጋምቢያ)
የአመቱ ምርጥ የእግርኳሱ መሪ
ማኑዌል ሎፔዝ ናሽሜንቶ የጊኒ ቢሳው እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት
የአመቱ ምርጥ 11
ዴኒስ ኦኒያንጎ (ዩጋንዳ)
ሰርጌ ኦሪየር (ኮትዲቯር) አይመን አብደኑር (ቱኒዚያ) ኤሪክ ቤሊ (ኮትዲቯር) ጆይስ ሎማሊሳ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)
ካማ ቢሊያት (ዚምባቡዌ) ሬንፎርድ ካላባ (ዛምቢያ) ኪገን ዶሊ (ደቡብ አፍሪካ)
ሪያድ ማህሬዝ (አልጄሪያ) ፒየር ኤምሪክ ኦባሚያንግ (ጋቦን) ሳድዮ ማኔ (ሴኔጋል)
ተጠባባቂዎች
አይመን ማትሉቲ (ቱኒዚያ) ፣ ካሊዱ ኩሊባሊ (ሴኔጋል)፣ ሳሊፍ ኩሊባሊ (ማሊ)፣ ኢስላም ስሊማኒ (አልጄሪያ)፣ መሃመድ ሳላ (ግብፅ)፣ ኬሌቺ ኢያናቼ (ናይጄሪያ)፣ አሌክ ኢዮቢ (ናይጄሪያ)