” እክሎች ካልተፈጠሩ በቀር የዮርዳኖስን ሪከርድ የግሌ ለማድረግ አስባለሁ” ጌታነህ ከበደ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ላይ ደርሷል፡፡ የደደቢቱ ግብ አዳኝ ጌታነህ ከበደም በ9 ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በመምራት ላይ ይገኛል፡፡ ጌታነህ በዚሁ የግብ ማግባት ስኬቱ እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ የሚዘልቅ ከሆነ በዮርዳኖስ አባይ በ24 ግብ የተያዘውና ለ17 የውድድር ዘመናት ያልተደፈረው በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ግብ የማስቆጠር ሪኮርዱን የማሻሻል እድል አለው፡፡

ጌታነህ ቡድኑ ደደቢት ከሜዳው ውጪ ከአርባምነጭ ነጥብ የተጋራበትን ግብ ካስቆጠረ በኋላ ስለ ወቅታዊ አቋሙ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

ከ3 አመት የደደቡብ አፍሪካ ቆይታ በኋላ ተመልሰሃል፡፡ ፕሪሚየር ሊጉን እንዴት አገኘኸው?

ሊጉ በጣም ጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ሁሉም ክለቦች ጠንካራ ፉክክር እያደረጉ መሆኑን አይቻለው፡፡ ክለቦች በገንዘብ አቅማቸው ተጠናክረዋል ፤ በየስታድየሙ ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ተመልካቾች ጨዋታዎችን እየተከታተሉ ይገኛሉ ። እንደ ችግር ያየሁት አንዳንድ የክልል ሜደዎች እንክብካቤ እየተደረገላቸው ካለመሆኑ የተነሳ ለመጫወት ምቹ አይደሉም ።ለምሳሌ የአርባምንጭ ስቴዲዮም በጣም ነው የተጎዳው በተረፈ ግን ብዙ የሆኑ ለውጦች አሉ።

ከክለቡ ስብስብ ጋር ያለህን ውህደት እንዴት ትመለከተዋለህ? ከ3 አመት ቆይታ በኋላ ስትመለስ አልቸገረኸም?

ደደቢት ትልቅ ቡድን ነው፡፡ ያለው ነገር ጥሩ ነው። ያው የቀድሞ ክለቤ እንደመሆኑ መጠን ከክለቡ ጋር ለመጣመር አልቸገረኝም፡፡ በጥሩ ቅንጅት አብረን እየሰራን እንገኛለን። ያለውም ስብስብ ካየኸው ብዙ ታዳጊዎች እያፈራ ይገኛል፡፡ የተወሰኑ ናቸው ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች ያሉት እንጂ አብዛኛዎቹ ታዳጊዎች ናቸው ። እንቅስቃሴያቸውም ተስፋ ሰጪ ሆኖ ነው ያገኘሁት ፤ በአጠቃላይ አሪፍ ቡድን ነው ።

የግብ እድሎችን ወደ ግብነት ለመቀየር ብዙም አትቸገርም፡፡ የዚህ ምስጢሩ ምንድን ነው?

እግር ኳስን የጀመርኩት ከ13 አመቴ ጀምሮ በፕሮጀክት ታቅፌ ነው፡፡ አድማሱ ገ/የስ በሚባል ጥሩ አሰልጣኝ ነው የሰለጠንኩት፡፡ የአጥቂዎች ጎል የማስቆጠር ብቃትን ቪዲዮ እያሳየ እንዴት ጎል ማስቆጠር እንዳለብኝ ያስተምረኝ ነበር፡፡ ያ ነገር አድጎ ነው ዛሬ ላይ የረዳኝ። አሁን ላይ ሜዳ ስመጣ ጎል እንደማስቆጥር እርግጠኛ ሆኜ ነው። ያም ይመስለኛል የአጨራረስ ብቃቴን ያሳደገው ብዬ አስባለው። ሌላው ጠንክሬ በመስራቴ ነው ሊሆን የሚችለው ።

እስካሁን በዘጠኝ ጨዋታ ዘጠኝ ጎል አስቆጥረሀል፡፡ ምን አልባት በዚህ አካሄድህ ለረጅም አመት በ24 ጎል ዮርዳኖስ አባይ የያዘውን ሪከርድ በዘድሮው የውድድር አመት መስበር ትችል ይሆን ?

አዎ፡፡ 2004 ላይ 20 ጎሎችን ሳስቆጥር ስምንት ጨዋታዎች ላይ በጉዳት መጫወት አልቻልኩም ነበር፡፡ የዛኔ ሙሉ ጤነኛ ሆኜ ብጫወት ኖሮ ሪከርዱን መስበር በቻልኩ ነበር፡፡ ተጨማሪም በ2005 በተመሳሳይ 22 ጎሎችን አስቆጥሬ ሁለት ጨዋታ እየቀረው ነበር ለሙከራ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናሁት እናም ያኔም መስበር እችል ነበር፡፡ ዘንድሮም ቢሆን እስካሁን በዘጠኝ ጨዋታ 9 ጎል አለኝ፡፡ ምን አልባት ከውጭ ሀገር ክለብ ጋር እየተነጋገርኩኝ ነው። ሁለተኛው ዙር ላይ አቋርጬ የማልሄድ ከሆነ አልያም ጉዳትና ሌሎች እክሎች ካልተፈጠሩ በቀር ዘንድሮ ይህን ታሪክ የግሌ ለማድረግ ጠንክሬ እሰራለው፡፡

በዘንድሮ የውድድር ዘመን ከደደቢት ጋር ምን ታስባለህ ?

ለዋንጫ ከሚፎካከሩ ክለቦች አንዱ ነን፡፡ ሊጉንም እየመራን እንገኛለን ፤ ጥሩ ነገሩ ደግሞ ሁለተኛ ዙር ላይ አብዛኛው ጨዋታ በሜዳችን እንደመጫወታችን መጠን አሁን ያለንን ጥሩ አቋም ይዘን በበለጠ አጠናክረን ዋንጫውን ለማንሳት እንሰራለን።

Leave a Reply