ቤኒናዊው የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ ሃሪሰን ሄሱ የሀገሩ ትልቁ የእግርኳስ ድረገፅ የሆነው ቢጄ ፉት (BJFOOT) በየዓመቱ በሚያዘጋጀው እና በውድድር ዘመኑ ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳዩ የቤኒን ዜጋ የሆኑ ተጫዋቾች በሚሸለሙበት ውድድር በሁለት የሽልማት ዘርፍ ዕጩ መሆን ችሏል።
ሃሪስተን በሽልማቱ የመጨረሻ ዕጩዎች ውስጥ መግባት የቻለው የዓመቱ ምርጥ ቤኒናዊ ግብ ጠባቂ እና የዓመቱ ምርጥ በአፍሪካ ውስጥ የሚጫወት ቤኒናዊ ግብ ጠባቂ በሚሉት ምድቦች ነው። ተጫዋቹ ለዚህ ሽልማት በዕጩነት ሲቀርብ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
በድረገፁ ላይ በሰፈረው መረጃ መሠረት ሐሪስተን በፈረንጆቹ 2016 ለክለቡ ኢትዮጵያ ቡና ካደረጋቸው ጨዋታዎች ውስጥ በ17ቱ ግብ ሳይቆጠርበት መውጣቱ እንዲሁም በአመቱ ባሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ በሽልማቱ የመጨረሻ ተመራጮች ውስጥ መግባት ችሏል።
ተጫዋቹ የዓመቱ ምርጥ ቤኒናዊ ግብ ጠባቂ በሚለው ዘርፍ በፈረንሳይ ሊግ 2 የሚጫወተው ሌ ሃቭር ክለብ ተሰላፊ ከሆነው ፋቢያን ፋርኖሌ እና በሌላው የፈረንሳይ ሊግ 2 ክለብ ቻሞይ ኒዮርቶ ከሚጫወተው ሳተርኒን ኣላግቤ ጋር የሚወዳደር ይሆናል። በቱኒዚያው ክለብ አፍሪካን የሚጫወተው ጃክዌስ ቤሳን እና የጋቦኑ ሴንተር ምቤሪ ሰፖርቲፍ ክለብ ግብ ጠባቂ የሆነው ጃማል ፋሳሲ የዓመቱ ምርጥ በአፍሪካ ሊግ የሚጫወት ግብ ጠባቂ በሚለው ምድብ የሃሪስተን ተፎካካሪዎች ናቸው።
የ23 ዓመቱ ግብ ጠባቂ የእግርኳስ ህይወቱን በሃገሩ ቤኒን ዳጄ ለሚባል ክለብ በመጫወት የጀመረ ሲሆን ኤኤስ ፖሊስ፣ ድራጎንስ ድ ኦውሜ እንዲሁም የኮንጎ ብራዛቪሉ ኤኤስ ቼሚኖትስ ሌሎች ሃሪስተን ተጫውቶ ያለፈባቸው ክለቦች ናቸው። በ2013ቱ የአልጄሪያው የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ እና በተወሰኑ የወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ የሀገሩን ማሊያ አድርጎ መጫወት የቻለው ሃሪስን ከ2008 ዓ.ም. መጀመሪያ አንስቶ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናን እያገለገለ ይገኛል።
የአንባቢዎች ምርጫ የሽልማቱን አሸናፊ ለመለየት ትልቅ ድርሻ ያለው ሲሆን ውድድሩን ባዘጋጀው ድረገፅ www.bjfoot.com/bjfoot-awards-2016 ላይ ድምፅ በመስጠት መሳተፍ እንደሚቻል ታውቋል።