ኮንፌድሬሽንስ ካፕ ፡ ‹‹ በተጋጣሚያችን አጨዋወት ላይ ተመስርተን ዝግጅት አድርገናል ›› ዮሃንስ ሳህሌ

ደደቢት ከናይዴርያው ዋሪ ዎልቭስ ጋር ለሚያደርገው የአንደኛው ዙር የመጀመርያ ጨዋታ በነገው እለት ወደ ስፍፍው የሚያመራ ሲሆን ከጉዞው በፊት የደደቢቱ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት የስልክ ቆይታ ስለ ዝግጅታቸው እና ስለተጋጣሚያቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከኮት ዲ ኦር ጨዋታ በኋላ ባሉት ቀናት ቡድናቸውን ለቀጣዩ ጨዋታ ሲያዘጋጁ የቆዩት አሰልጣኝ ዮሃንስ ስለ ተጋጣሚያቸው ‹‹ ስለ ናይጄርያው ቡድን ጥቂት መረጃዎችን ሰብስበናል፡፡ የሊግ ውድድራቸው ገና መጀመሩ በመሆኑ ከወር በፊት ያደረጉትን ጨዋታ ቪድዮ ተመልክተናል፡፡ በዚህም መሰረት አጨዋወታቸው ላይ ትኩረት አድርገን ተዘጋጅተናል፡፡ ቡድኑ ከዚህ በፊት በኮንፌድሬሽን ዋንጫ ልምድ ያለው በመሆኑ ጨዋው ሊከብድ ቢችልም ጥሩ ዝግጅት በማድረጋችን ከሌጎስ ጥሩ ውጤት ይዘን እንመለሳለን ብለን እናምናለን፡፡

ደደቢት በቅድመ ማጣርያው 5 ግቦችን ቢያስቆጥርም አሁንም የአጥቂ ክፍሉ ገና ብዙ እንደሚቀረው አሰልጣኙ ያምናሉ፡፡ ‹‹ የአጨራረስ ድክመት አለብን፡፡ የአጥቂ ተጫዋቾች እጥረት ያለብን ከመሆኑም በላይ እንዲህ አይነት ችግሮች በአንድ ጊዜ የሚፈቱ አይደሉም፡፡ በዚህም ምክንያት ከነ አጥቂ ክፍተታችን ወደ ሌጎስ አናመራለን፡፡ ›› ሲሉ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

በተያያዘ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ በተጫዋቾች ግዢ ላይ የተቀዛቀዘው ደደቢት ከወጣት ቡድኑ 7 ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን በማሳደግ በሁለተኛው ዙር የሊግ ውድድር እንደሚጠቀሙባቸው አሰልጣኙ ተናግረዋል፡፡

ያጋሩ