ኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ኒቦሳ ቩሲቪችን አሰናበተ

ኢትዮጵያ ቡና ሰርቢያዊውን የክለቡ አሰልጣኝ ኒቦሳ ቩሲቪችን ማሰናበቱን በፌስቡክ ገፁ ይፋ አድርጓል፡፡ 

በዓመቱ መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የመጡት ቩሲቪች በአሰልጣኝነት መንበር በቆዩባቸው ጊዜያቶች ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማሸነፍ የቻለው ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ነበር፡፡ ጫና ውስጥ የነበሩት ቩሲቪች የውጤት ቀውስ ውስጥ ክለቡን መጣላቸው ከአሰልጣኝነት የመነሳታቸው ዋነኛው ምክንያት ሊሆን ቢችልም ኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኙ የተነሰቡበትን ዋና ምክንያት በቀጣይ ቀናት እንደሚገልፅ ተናግሯል፡፡ በአፍሪካ እግርኳስ እምብዛም የመስራት ልምድ የሌላቸው የቀድሞ የፓርቲዛን ቤልግሬድ ተጫዋች ከዚህ ቀደም በጋናው አክራ ሃርትስ ኦፍ ኦክ ከወራት ቆይታ በኃላ የተሰናበቱ ሲሆን የኢትዮጵያ ቆይታቸውም ልክ እንደጋናው ሁሉ ሳይሰምር ቀርቷል፡፡

ሌላኛውን ሰርቢያዊ አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲችን ተክተው  ወደ ኢትዮጵያ ቡና የመጡት ቩሲቪች በ9ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በወልዲያ መልካቆሌ ላይ 1-0 የተሸነፉበት ጨዋታ የመጨረሻቸው ሆኖ አልፏል፡፡

አሰልጣኝ ቩሲቪች ሰኞ ጠዋት የክለቡ መደበኛ ልምምድን መምራት መቻላቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ማረጋገጥ ችላለች፡፡

ተሰናባቹ አሰልጣኝ ቩሲቪችን ተክተው ረዳት አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ እና ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ እድሉ ደረጄ በጊዜያዊነት ዋና ቡድኑን ይመሩታል፡፡

አሰልጣኝ ገዛኸኝ በክለቡ ለረጅም ግዜ የቆዩ ሲሆን በምክትል አሰልጣኝነት እና በታዳጊ ቡድኑ አሰልጣኝነት ክለቡን ማገልገል ችለዋል፡፡ የቀድሞው የቡድኑ አምበል እድሉ በዓመቱ መጀመሪያ ከ20 ዓመት በታች ቡድኑን ሲመራ የቆየ ሲሆን የቩሲቪችን ስንብት ተከትሎ ወደ ምክትል አሰልጣኝነት ቦታ መጥቷል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አሰልጣኝ እየተመራ ማክሰኞ ሃዋሳ ከተማን አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ያስተናግዳል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዓመቱ የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረገ ሁለተኛው የሊጉ ክለብ ነው፡፡ ደደቢት ከዚህ ቀደም ዩሃንስ ሳህሌን ማሰናበቱ ይታወሳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *