የጨዋታ ሪፓርት | ኢትዮጵያ ቡና ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

በ10ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሰልጣኝ ኒቦሳ ቪሴቪችን ያሰናበቱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በሜዳቸው እና በደጋፊዎቻቸው ታግዘው ሀዋሳ ከተማን 2-1 ማሸነፍ በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሰዋል፡፡

በቀድሞው ምክትል አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ እና እድሉ ደረጀ እየተመሩ ወደ ሜዳ የገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ባሳለፍነው አርብ በወልዲያ ከተሸነፈው ቡድን የተጫዋቾች እና የጨዋታ አቀራረብ ለውጦች አድርገው ነበር ጨዋታውን የጀመሩት፡፡

በጨዋታውም ሀዋሳ ከተማዎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንዲሁም በአሁኑ ሰአት በግብፅ ሊግ ለሚገኘው ፔትሮጄት በመጫወት ላይ በሚገኘው የቀድሞው ልጃቸው ሽመልስ በቀለ ከሀገረ ግብፅ አሰርቶ ያመጣውን አዲሱን ነጭ መለያ ለብሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ተጫውተዋል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡

በ7ኛው ደቂቃ ላይ እያሱ ታምሩ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ አስቻለው ግርማ ከተቆጣጠረ በኃላ ከፍፁም ቅጣት ክልል ጠርዝ ላይ አክርሮ በመምታት በቀድሞ ክለቡ ላይ ማራኪ ግብን ማስቆጠር ችሏል ፤ ከግቧ መቆጠር በኃላ አስቻለው ለቀድሞ ክለቡ ክብር ለመስጠት በሚመስል መልኩ ደስታውን ሳይገልፅ ቀርቷል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ሁለተኛዋን ግብ እስኪያስተናግዱ ድረስ የተሻለ ኳስን ተቆጣጥረው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ  ሲሞክሩ ተስተውሏል ፡፡ በነዚህም ደቂቃዎች ከተደረጉት ሙከራዎች መሀከል በ15ኛው ደቃቃ ላይ ፍሬው ከርቀት ሞክሮ ሀሪስተን የመለሰውን ኳስ ዳግም ኤፍሬም ዘካሪያስ ሞክሮ ኤፍሬም ወንደሰን ሸርፎ ያወጣበት እንዲሁም በ20ኛው ደቂቃ ጋዲሳ መብራቴ በግራ መስመር አቅጣጫ ወደ ግብ ክልል ውስጥ ከገባ በኃላ ወደ መሀል ያቀበለውና መድሀኔ ታደሰ ያመከነው ኳስ ተጠቃሾች ነበሩ፡፡

ከነዚህም በተጨማሪ ሀዋሳ ከተማዎች በርከት ያሉ የቆሙ ኳሶችን በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት የኢትዮጵያ ቡናው ግብጠባቂ ሀሪሰንን ሲፈትኑት አምሽተዋል፡፡ ጋዲሳ መብራቴ በ11ኛው እና በ26ኛው ፤ በ31ኛው ደቂቃ ላይ እንዲሁ ጃኮ አራፋት በቀጥታ መትተው ሀሪስተን ያዳናቸው ኳሶችም ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡

በ22ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አስቻለው ግርማ በግራ መስመር አቅጣጫ ፍጥነቱን እና የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ለመግባት ጥረት ሲያደርግ በሀዋሳ ተከላካዮች በመጠለፉ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ጋቶች ፓኖም ወደ ግብነት ቀይሯት ቡድኑን 2-0 መሪ ማድረግ ችሏል፡፡

 ከሁለተኛዋ ግብ መቆጠር በኃላ በነበሩት የተቀዛቀዙ የጨዋታ ሂደቶች ውስጥ በ39ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ሀሰን ከቀኝ መስመር ያሻማውና ጋቶች ገጭቶ ኢላማውን ሳይጠብቅ ከቀረው ኳስ ውጪ ተጠቃሽ ሙከራ ሳይታይ የመጀመርያው አጋማሽ በቡና መሪነት ተገባዷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ሰከንዶች ኤፍሬም ዘካሪያስ ከጋዲሳ ተቀብሎ ከርቀት አክርሮ የመታት እና ሀሪሰን የያዛት ኳስ ጥሩ ሙከራ ነበረች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የበለጠ በማጥቃት ለመጫወት የሞከሩት ሀዋሳ ከተማዎች በ48ኛው ደቂቃ ላይ በጃኮ አራፋት እና መድሀኔ ታደሰ በተከታታይ ወደ ግብ ሞክረው ማስቆጠር ያልቻሏቸው ኳሶች የሚያስጩ ነበሩ፡፡

በ53ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ዮሀንስ በፈጣን ከመከላከል ወደ ማጥቃት በተደረገ ሽግግር የተገኘውን ኳስ ለያቡን አቀብሎት ያቡንም የሞከረው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትማ ወደ ውጪ የወጣችው ኳስ የቡናን መሪነት ወደ 3-0 ማሳደግ የምትችል አጋጣሚ ነበረች፡፡

በአንጻሩ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከፍተኛ ፍላጎት ሲያሳዩ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በ54ኛው ደቂቃ በሀሪሰን የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታግዘው ያገኙትን ግብ የማግባት አጋጣሚ ጃኮ አራፋት ቢሞክርም ወንድይፍራው ጌታሁን ከግቡ መስመር ላይ ሊያወጣበት ችሏል፡፡ ሆኖም የቡድኑ አምበል ደስታ ዮሃንስ በ60ኛው ደቂቃ ላይ መድሀኔ ታደሰ ያሻማለትን ኳስ በመግጨት ቡድኑን ወደ ጨዋታው ልትመልስ የምትችለውን ግብ አስቆጥሯል፡፡

ከአንድዋ ግብ መቆጠር በኃላ ሀዋሳ ከተማዎች በተሻለ የመሀል ሜዳውን ብልጫ በመውሰድ ጫና በመፍጠር የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ዳግም ኢትዮጵያ ቡናዎች በ64ኛው ደቂቃ አማኑኤል ዮሀንስ ከግብ ክልሉ  ጨረቃ ላይ ሞክሮ ሜንሳ ያዳነበት እንዲ እንዲውም በ67ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም አሾልኮ አስቻለው ለጥቂት ሳይደርስበት ቀርቶ የባከኑት አጋጣሚዎች ኢትዮጲያ ቡና ዳግም የጎል ልዮነቱን ወደ ሁለት ማስፋት የሚችልባቸው እድሎች ነበሩ፡፡

በ73ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አብዱልከሪም ሀሰን በአክሊሉ ዋለልኝ ተቀይሮ በሚወጣ ሰአት እጅግ በርካታ የሚባሉ የቡና ደጋፊዎች በአሰልጣኝ ቡድናቸው ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

በ83ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታው አነጋጋሪ ክስተት ተከስቷል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከመሀል የላኩትን ኳስ አማኑኤል ዮሀንስ የሀዋሳው ግብጠባቂ መውጣቱን ተመልክቶ  ከአናቱ በላይ የላካትን ኳስ ከግቡ መስመር ላይ የነበረው ወንድማገኝ ማአረግ ያወጣትን ኳስ መስመራን አልፋለች በሚል የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ቡናዎች የክስ ሪዘርቨ አስይዘው ጨዋታው ቀጥሏል፡፡

በ93ኛደቂቃ ላይ ተቀይሮ ከገባው ሳዲቅ ሴቾ የተቀበለውን ኳስ አስቻለው ግርማ በሀዋሳዎች የግብ ክልል ውስጥ ግብጠባቂውን ሜንሳን ለማለፍ ሲጥር ተጠልፎ በመውደቁ የተገችውን የፍፁም ቅጣት ምት ሳዲቅ ሴቾ ቢመታም ኳሷ የግቡን ቋሚ ለትማ ወጥታለች፡፡ ጨዋታውም በቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች በተለይም ግብ ጠባቂው ሜንሳህ በዳኛው ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ተቋውማቸውን ሲያሰሙ እና ሲያዋክቡ ተስተውሏል፡፡

ኢትዮጲያ ቡና በዛሬው ድል በመታገዝ ነጥቡን ወደ 13 ከፍ ማድረግ ሲችል በአንጻሩ ተሸናፊዎች ሀዋሳ ከተማዎች አሁንም በወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ፡፡

Leave a Reply