የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትላንት ምሽት አንድ ተስተካካይ ጨዋታ አስተናግዶ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደደቢትን ረቷል፡፡ ጨዋታው በሁለት ታላላቅ ቡድኖች መካከል የተካሄደ በመሆኑ በበርካቶች በጉጉት እንዲጠበቅ ቢያደርግም ከጨዋታው መጀመር በፊት መጣል የጀመረው ከባድ ዝናብ ጨዋታውን እንዳያስተጓጉለው ተፈርቶ ነበር፡፡
አሰልጣኝ ማርት ኑይ ደጉ ደበበን የተከላካይ አማካይነት ሚና ሲሰጡት አዳና ግርማን ወደ ፊት አስጠግተው አጫውተውታል፡፡ ካለ ዳዊት ፍቃዱ እና አዳሙ መሃመድ ወደ ሜዳ የገቡት አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ደግሞ በሁለቱ ምትክ ዘነበ ከበደ እና አሸናፊ አደምን በቋሚ አሰላለፉ አካተዋል፡፡
በመጀመርያው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተደጋጋሚ ወደ ግብ መድረስ ሲችል ኡመድ ኡኩሪ እና ሳሙኤል ሳኑሚ በተደጋጋሚ የታሪኩ ጌትነትን ግብ ለመድፈር ጥረት አድርገዋል፡፡ በተለይም ኡመድ ኡኩሪ ከቅጣት ምት አክርሮ የመታት ኳስ በጥሩ የግብ እድልነት የምትጠቀስ ነበረች፡፡ በ26ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳኑሚ ግብ ቢያስቆጥርም ረዳት ዳኛው በአወዛጋቢ ሁኔታ ከጨዋታ ውጪ ምልክት አሳይተዋል፡፡ በዚህ 45 ደቂቃ ደደቢት በመከላከሉ የተሸለ የነበረ ቢሆንም ወደ ግብ መድረስ የቻሉባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ የነበረው ፉክክር ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አመዝኖ በ63ኛው ደቂቃ አዳነ ግርማ ከኡመድ ኡኩሪ የተሸገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ቅዱስ ጊዮርጊስን መሪ አድርጓል፡፡ ለመጀመርያው ግብ መገኘት አስተዋፅኦ ያደረገው ኡመድ ኡኩሪ የቅዱስ ጊዮርጊስን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ያደረጋትን ግብ በ78ኛው ደቂቃ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሯል፡፡
ደደቢቶች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጉት ጥረት እምብዛም ፍሬያማ አልነበረም፡፡ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር አማካይ መስፍን ኪዳኔ ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ በ86ኛው ደቂቃ ግብ አስኪያስቆጥር ድረስም ይህ ነው የሚባል የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሉ በኋላ በ13 ጨዋታዎች በ1ዱ ብቻ ተሸንፎ 12 አሸንፎ 29 ግቦች ከመረብ አሳርፎ 6 ግቦች ብቻ ተቆጥረውበት በ36 ነጥቦች የመጀመርያውን ዙር በመሪነት አጠናቋል፡፡ አሰልጣኝ ማርት ኑይም በድል የቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታቸውን አሳርገዋል፡፡
ደደቢት በበኩሉ 2 ቀሪ ጨዋዎች በእጁ ያሉት ሲሆን መጋቢት 25 ከሀዋሳ ከነማ መጋት 29 ደግሞ ከወላይታ ድቻ ጋር ከባድ ፍልሚያ ይጠብቀዋል፡፡
ከደደቢት በተጨማሪ ኢትዮጵያ ቡና ከሐረር ቢራ ረቡእ መጋቢት 24 የሚያደርገው ጨዋታ ሌላው የ1ኛው ዙር ተስተካካይ መርሃ ግብር ነው፡፡
{jcomments on}