ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ወልድያ | የአሰልጣኞች አስተያየት 

ማርት ኖይ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው ከባድ ነበር። ሜዳውም ትንሽ እርጥበት ይዞ ስለነበር ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ይከብድ ነበር። ግን የግብ ዕድሎችን ማግኘት ችለናል። ግብ ለማስቆጠር ከነበረው ጉጉት አንፃር አንዳንድ ተጫዋቾች ላይ የመረጋጋት ችግር ይታይ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ተጭነን መጫወት እና ቶሎ ቶሎ ወደግብ መድረስ ስለቻልን በርካታ የግብ አጋጣሚዎች እንድናገኝ አድርጎናል። በመጨረሻም 1-0 አሸንፈናል። በደረጃ ሰንጠረዡም ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለናል። ጥሩ ተጫውተናል ብዬ አስባለሁ። በመከላከል ላይ የተመሰረተ አጨዋወት የሚከተል ቡድን ጋር ስለተጫወትን ነገሮች ቀላል አልነበሩም።”

ቡድኑ በጨዋታው ስላሳየው አቋም

“ተጫዋቾቼ ግብ  ለማስቆጠር የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። ማድረግ የሚገባውን ሳያደርግ ቀረ ብዬ ቅር የተሰኘሁበት ምንም ተጫዋች የለም። ግን እንዳልኩህ ተጫዋቾቹ አንዳንድ ጊዜ ግብ ለማስቆጠር በጣም ስለሚጥሩ ባላቸው ጉጉት ምክኒያት የግብ ዕድሎችን መጠቀም አልቻሉም ነበር።”

የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ስላሰሙት ተቃውሞ

“ይህ የሆነው በጨዋታው በነበረው ውጥረት ምክንያት ነው። ሁሉም ግብ ለማስቆጠር ይፈልግ ነበር። ተጫዋቾቹ፣ አሠልጣኙ፣ ረዳት አሠልጣኞቹ፣ የቡድን መሪው እና ደጋፊዎቹ ሁሉ ወደሜዳ ገብተው ግብ ማስቆጠር ቢችሉ ይደሰቱ ነበር። በመጨረሻ ግብ ስናስቆጠር ግን ሁሉም ደስተኛ ነበር።”

ቡድኑ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ማሻሻል ስለመቻሉ

“ትክክለኛ ቦታችን በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ነው።”

ንጉሴ ደስታ – ወልዲያ

ስለጨዋታው

“የዛሬው ጨዋታ በጣም ጥሩ ነበር። በተጫዋቾቼ በጣም ረክቻለው፤ ጥሩ እንቅስቃሴ ነው የነበረው። በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ያገኘናቸውን የግብ አጋጣሚዎች ብንጠቀም ኖሮ አሸናፊ ሆነን የምንወጣበት ዕድል ነበረን። ቢሆንም በሁለተኛው 45 ደቂቃ በትኩረት ማጣት ምክኒያት ያጋጠማቸውን ዕድል ተጠቅመው ጎል አግብተውብናል። ይህም ሆኖ ግን በቡድኑ ደስተኛ ነኝ።”

በጨዋታው ማግኘት አቅደው ስለነበረው ውጤት

“ቡድኔ ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ እየመጣ ነው። ስለዚህ ወደ ጨዋታው ስንመጣ አሸንፈን ደረጃችንን እናሻሽላለን ብለን ነበር የመጣነው። ጊዮርጊስ ካለው ልምድ አንፃር እንጂ መሸነፍ የሚችል ቡድን ነው።”

ቡድኑ ስላለበት ግብ የማስቆጠር ችግር

“የጎል ማግባት አቅማችን ደካማ ነው፤ አሁንም እዚህ ላይ በጣም መስራት ይኖርብናል። የቅድመ ውድድር ዝግጅት ጊዜያችን አጭር ስለነበር የሚያስፈልጉንን ተጫዋቾች በቡድናችን ማካተት አልቻልንም ነበር። በውድድር ዘመን አጋማሽ የዝውውር ጊዜ ይህን እናስተካክላለን ብለን እናስባለን።”

ስለ ዳኝነቱ

“ዳኝነቱ በጣም የሚጋነን ባይሆንም ትንሽ ጫና እኛ ላይ ፈጥሯል። ዳኛውን መውቀስ አልፈልግም፤ ነገርግን ሁለቱን ቡድኖች እኩል ያለማየት ነገር ነበር።”

ስለ አዲሱ የወልዲያ ስታዲየም

“አዲሱ ስታዲየም ለወልዲያ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለሀገሪቷ የሚጠቅም ትልቅ እና ዘመናዊ የሆነ ስታዲየም ነው። በዚህ ስታዲየም ላይ መጫወት መቻላችን ለቡድናችን ትልቅ አቅም ይፈጥራል። ጥሩ ሜዳ ካገኘ ኳስ መጫወት የሚችል ቡድን ስላለን የተሻለ ተጠቃሚ እንሆናለን ብለን እናስባለን።”

1 Comment

  1. ወልድያ በየትኛውም መስፈርት የተሻለ ነበረ ማለት ይቻላል ግን ጊዮርጊሶች ልምዳቸውን ተጠቅመው ወሳኙን 3 ነጥብ ይዘው ወጥተዋል። በክልል ቡድኖች ያየሁት መሻሻል ግን ይበል የሚያስብል ነው፡ በዚህ ከቀጠሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ የበላይነቱን እንደሚወስዱ አመላካች ነው።

Leave a Reply