የጋቦን 2017 ተሳታፊዎች ፕሮፋይል | ዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን [ክሬንስ]

ከ39 ዓመታት በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የተመለሱት ዩጋንዳዎች ብቸኛዎች የምስራቅ አፍሪካ ወኪል ናቸው፡፡ 

ክሬንስ በሚል ተቀፅላ ስም የሚታወቁት ዩጋንዳዎች በምስራቅ አፍሪካ እግርኳስ በተደጋጋሚ የሴካፋ ቻምፒዮን ቢሆኑም ከ1978 ወዲህ አፍሪካ ዋንጫ ጋር ተለያይተው ቆይተዋል፡፡ በ2012 በኬንያ በ2013 ደግሞ በዛምቢያ ተሸንፈው ከአፍሪካ ዋንጫው ውጪ ሆነዋል፡፡ ለአብዛኞቹ የዩጋንዳ አፍቃሪያን ከረጅም ግዜ ቆይታ በኃላ ያሳኩት የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የ2016 የግሎ ካፍ ምርጥ የወንዶች ብሄራዊ ቡድን ከተሰኘው ቡድናቸው ብዙ ይጠብቃሉ፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – 6

ተጠቃሽ ውጤት፡ አራተኛ (1962) ፣ ሁለተኛ (1978)

አሰልጣኝ፡ ሰርዮቪች ሚሉቲን ሚቾ

ዩጋንዳ በምድብ አራት ከጋና፣ ማሊ እና ግብፅ ጋር ተመድባለች፡፡ ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሚቾ ቡድናቸው ስለሚገጥመው ፈተና በማሰብ በይበልጥ በተጫዋቾች ስነ-ልቦና እና ራስ-መተማመን ላይ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ክሬንሶቹ ስሎቬኒያን እና ስሎቫኪያን በአቋም መለኪያ የገጠሙበት ምክንያት ይህ ነው፡፡ ዩጋንዳ ምንም እንኳን በቱኒየዚያ 2-0 ሽንፈትን ብታስተናግድም ከመጀመሪያ ተጋጣሚዋ ጋና በተሻለ የአቋም መለኪያ ማድረግ ችላለች፡፡ ዩጋንዳ በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ሽንፈትን እና ግብ ያላስተናገደ ቡድን ያላት ሲሆን ሚቾ በ2013 ከመጡ ወዲህ ከጋና ጋር ባደረጉት ሶስት ጨዋታዎች አልተሸነፉም፡፡

የዩጋንዳው ክለብ ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶሪቲ የሚዲያ እና የማስታወቂያ ሃላፊ፣ የKawowo.com እንዲሁም የዴይሊ ሞኒተር ዩጋንዳ ጋዜጣ ፀሃፊ የሆነው ክሊቭ ካያዚ ስለሃገሩ የአፍሪካ ዋንጫ ተስፋ እና ስጋት የሚከተለውን ለሶከር ኢትዮጵያ ብሏል፡፡

ስለምድብ አራት

“ዩጋንዳ አስቀድሞውንም ቀላል ምድብ እንደማታገኝ የታወቀ ነው፡፡ ከረጅም ግዜ በኃላ እንደመመለሳችን የትኛውም ምድብ ለእኛ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ የመደብነው ከሶስት የውድድር ልምድ ካላቸው ሃገራት ጋር መሆኑ ምድቡን ጠንካራ ያደርገዋል፡፡ ከጋና ጋር ከዚህ ቀደም ተጫውተን በባለፉት አራት ጨዋታዎች አልተሸነፍንም፡፡ ቢሆንም ይህ ማጣሪያ ሳይሆን ውድድር ነው፡፡ አውቃለው ጋናዎች ከባለፈው የፍፃሜ ሽንፈታቸው ህመም ላይ እንደሚገኙ፡፡ ግብፅም ከ2010 በኃላ ብትመለስም ቀላል ተጋጣሚ አትሆንም፡፡ በተለይ ደግሞ ዩጋንዳ ከሰሜን አፍሪካ ሃገራት ጋር ስትጫወት ስለምትቸገር ነገሮች ቀላል አይሆንም፡፡ከፈንሳይኛ ተናጋሪ የአፍሪካ ሃገራትም ጋር ትቸገራለች፡፡ ማሊ እንደጋና እና ግብፅ ሁሉ የውድድር ቡድን ነው፡፡ ከምድቡ የሚወጡበትን መንገድ የሚያውቁ ይመስላሉ፡፡”

ተስፋ

“በአንዳንድ ምክንያቶች ከምድቡ እንደምናልፍ አምናለሁ፡፡ ጋናን በማሸነፍ፣ ከግብፅ እና ማሊ ጋር ያልተጠበቀ አቻ በመያዝ አምስት ነጥብ ይዘን ከምድቡ የምናልፍ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን አንድ የተለየ ነገር ከተጫዋቾቹ ያስፈልጋል፡፡ የአመቱ ምርጥ ቡድን መባላችን እንዲሁም የኦኒያንጎ ውጤታማነት ቡድኑን ያነሳሳል ያም ቢሆን በጫና ውስጥ ሆነን ነው፡፡”

ስጋቶች

“የተለየ ስጋት ብዬ ማስበው የመስመር ተከላካዮቻችን በሜዳ ላይ የሚኖራቸው ድርሻን ነው፡፡ ወደፊት ተጭኖ መጫወት እና ማጥቃትን ይወዳሉ ጨዋታ ማንበብ ላይ ግን እጅግ የወረዱ ናቸው፡፡ ነገሮችን ያባባሱት ደግሞ ሚቾ የሚጠቀማቸው ሶስት የተከላካይ አማካዮች የመስመር ተከላካዮቹ ለማጥቃት ሲሄዱ የተዉትን ቦታ አለመሸፈናቸው ነው፡፡ በአለም ዋንጫው ማጣሪያ ከጋና ጋር ይህ በጣም ግልፅ ነው እንዲያውም ጋናዎች ይህንን ክፍተት ተጠቅመው እኛን አለመቅጣታቸው ዕድለኛ ያስብለናል፡፡ እንድ ማሊ እና ግብፅ ያሉ ቡድኖች ጋር ግን ዕድለኛ አንሆንም፡፡”

የሚጠበቅ ተጫዋቾች

“ከኦኒያንጎ በኃላ ፋሩክ ሚያን እመርጣለው፡፡ ለዩጋንዳ የተለየ ነገር የሰራ እና በመስራት ላይ የሚገኝ ጥሩ ተጫዋች ነው፡፡ ወሳኝ የግብ ማግባት ምንጫችን ጂኦፍሪ ማሳ ግብ ማምረት ባቆመበት ወቅት ሚያ ሃላፊነቱን በሚገባ ተውጥቷል፡፡ ሌላው ቶኒ ማዊጄ ነው፡፡ አሁን ላይ ፊትነሱ ጥሩ አይደለም ነገር ግን ጨዋታዎች የመወሰን ብቃት አለው በሚሰጠው የተመቻቸ ኳስ እና በሚስቆጥራቸው ግሩም ግቦች፡፡ ሁለቱ የክንፍ ተጫዋቾች ሞሰስ ኦሎያ እና ኪዚቶ ሉዋጋ ጥሩ ናቸው፡፡ በደጋፊ የሚወደድ ጨዋታ መጫወታቸው እንዲወዱ ያደርጋቸዋል፡፡”

ሚቾ በቡድናቸው ስብጥር ውስጥ ዴኒስ ኦኒያጎን የመሰለ ግብ ጠባቂ ይዘዋል፡፡ የአፍሪካ ምርጡ ግብ ጠባቂ ተብሎ የሚሞካሸው ኦኒያንጎ ዓመቱን በተሳካ ሁኔታ አጠናቅቋል፡፡ በተጠባባቂነት በጥሩ ብቃታቸው የሚታወቁትን ሮበርት ኦዶንካራ እና ጀማል ሳሊምን ይዘዋል፡፡ ሚቾ ቅድሚያ ጥንቃቄ ወስደው የሚጫወት ቡድን በዩጋንዳ የመገንባታቸው ሚስጥር የተከላካዮቹ ጥራት አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ የተለቀቀው አይዛክ ኢዜንዴ የቡድኑ አካል ሲሆን ለአንድ ዓመት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቆይታ የነበረው ሃሰን ዋሳዋም ይበልጥ የተከላካይ ክፍሉን ሽፋን በመስጠት ያጠነክረዋል፡፡ ከፊት የሚያ እና ማሳ ጥምረት ሲጠበቅ የዩጋንዳ የ2016 የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች መሃመድ ሻባን ግብ ለማስቆጠር የሚከብደው አይመስልም፡፡ አብዛኞቹ ተጫዋቾች አሁን ካሉበት ደረጃ በላይ የተሻለ ክለብ ለማግኘት የአፍሪካ ዋንጫው እንደመሸጋገሪያ ከተጠቀሙበት እውነትም ዩጋንዳ አስገራሚዋ የአፍሪካ ዋንጫ ቡድን መሆኗ አይቀርም፡፡

የማጣሪያ ጉዞ

ዩጋንዳ በማጣሪያው ከቡሪኪናፋሶ፣ ኮሞሮስ እና ቦትስዋና ጋር በምድብ አራት ተደልድላ ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹን ሁለት የመክፈቻ ጨዋታዎች ኮሞሮስን እና ቦትስዋናን በማሸነፍ የጀመረችው ዩጋንዳ በተከታታይ በቡርኪናፋሶ የጣለቻቸው ነጥቦች የማለፍ ተስፋዋን ጥያቄ ውስጥ ከተው ነበር፡፡ ዩጋንዳ በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ድል በማድረግ ለአፍሪካ ዋንጫ የበቃችው በጥሩ ሁለተኛነት ነው፡፡ ክሬንሶቹ ኮሞሮስን የረቱበትን የመጨረሻ የማጣሪያ ጨዋታ ግብ ያስቆጠረው ልማደኛው ፋሩክ ሚያ ነው፡፡ ከስድስት ጨዋታ በአራቱ ስታሸንፍ በአንድ አቻ ወጥታ በአንድ ተሸንፋለች፡፡

ሙሉ ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

ዴኒስ ኦኒያንጎ (ማሜሎዲ ሰንዳውንስ/ደቡብ አፍሪካ)፣ ሮበርት ኦዶንካራ (ቅዱስ ጊዮርጊስ/ኢትዮጵያ)፣ ጀማል ሳሊም (ኤል-ሜሪክ/ሱዳን)

ተከላካዮች

አይዛክ ኢዜንዴ (ክለብ የለውም)፣ ጂኦፍሪ ከዚቶ (ታን ኩዋንግ ኒን/ቬትናም)፣ ጆሴፍ ኦቻያ (ኬሲሲኤ/ዩጋንዳ)፣ ሙሩሺድ ጁኮ (ሲምባ/ታንዛኒያ)፣ ዴኒስ ኢጉማ (አል አሃድ/ሊባኖስ)፣ ዋኪሮ ዋዳዳ (ቫይፐርስ/ዩጋንዳ)፣ ቲሞቲ አዋኒ(ኬሲሲኤ/ዩጋንዳ)፣ ሻፊክ ባታምቡዚ (ተስካር/ኬንያ)

አማካዮች

ቶኒ ማዊጄ (ትሮትር ሬክያቪክ/አይስላንድ)፣ ካሊድ አዉቾ (ባሮካ/ደቡብ አፍሪካ)፣ ኪዚቶ ሉዋጋ (ሪዮ አቬ/ፓርቹጋል)፣ ሞሰስ ኦሎያ ((ቲቲ ሃ ኖይ/ቬትናም)፣ ጎድፍሬ ዋሉሲምቢ (ጎር ማሂያ/ኬንያ)፣ ሃሰን ዋሳዋ (ኒጅማሃ/ሊባኖስ)፣ ማይክል አዚራ (ኮሎራዶ ራፒድስ/ዩናይትድ ስቴትስ)

አጥቂዎች

የኑስ ሴንታሙ (አይአይቪኢኤስ/ፊንላድ)፣ ጅኦፍሪ ሴሬንኩማ (ኬሲሲኤ/ዩጋንዳ)፣ ጂኦፍሪ ማሳ (ባሮካ/ዩጋንዳ)፣ ፋሩክ ሚያ (ስታንዳርድ ሊየዥ/ቤልጂየም)፣ ሙሃመድ ሻባን (ኦንዱፓራካ/ዩጋንዳ)

ዩጋንዳ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ጋናን በዕለት ማክሰኞ በመግጠም ትጀምራለች፡፡

Leave a Reply