የጋቦን 2017 ተሳታፊዎች ፕሮፋይል | ግብፅ ብሄራዊ ቡድን [ፈርኦኖቹ]

ፈርኦኖቹ ከሶስት የአፍሪካ ዋንጫ ቆይታ በኃላ ወደ ነገሱብት የአህጉሪቱ ውድድር ዳግም ተመልሰዋል፡፡

በአብዛኛው በሃገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ብቻ በመያዝ ለሶስት ተከታታይ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ክብርን በብቸኝነት የያዙት ግብፆች እግርኳሳቸው በ2011 የፖለቲካ አለመረጋጋት ክፉኛ ተጎድቶ ነበር፡፡ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመመለስም ሰባት ዓመታት ፈጅቶባቸዋል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – 23

ውጤት፡ ሰባት ግዜ ቻምፒዮን (1957፣ 1959፣ 1986፣ 1998፣ 2006፣ 2008 እና 2010)

አሰልጣኝ፡ ሄክቶር ኩፐር

ግብፅ በምድብ አራት ከጋና፣ ማሊ እና ግብፅ ጋር ተደልድላለች፡፡ ከቅርብ ግዜያት ወዲህ እየተሻሻለ የመጠው ብሄራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ይሁን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች የማይቀመስ ሆኗል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት በአቋም መለኪያ ጨዋታ ቱኒዚያን 1-0 ያሸነፈው የሄክቶር ኩፐሩ ቡድን የሚከላከል ቡድን ነው ብለው የሚተቹት ብዙዎች ናቸው፡፡ በመልሶ ማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጨዋወትን የሚተገብሩት አርጀንቲናዊው አሰልጣኝ እስካሁን መልካም የሆነ ውጤት ለፈርኦኖቹ ይዘው መጥተዋል፡፡

የArqam እና kingfut.com ፃሃፊ እንዲሁም የተጫዋቾች መልማይ የሆነው ሂሻም አቦዘርኪ ስለግብፅ የአፍሪካ ዋንጫ ተስፋ፣ ስጋት እና ሌሎችንም የሚከተለውን ብሏል፡፡

ስለምድብ አራት

“ምድቡ ትንሽ አሳሳች ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ምድብ ውስጥ ካሉ ሶስት ሃገራት ሁለቱ ከእኛ ጋር በአለም ዋንጫው ማጣሪያ የሚገኙ ናቸው፡፡ በእርግጥ ለአሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ቡድኖቹን ለማጥናት ቀላል ይመስላል፡፡ ቢሆንም ከፍተኛ የአዕምሮ ስራን ይጠይቃል ምክንያቱም የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ውጤታችን በእዚህ ላይ ይንፀባረቃል፡፡ ቢሆንም ጋናን በመጨረሻ የምድብ ጨዋታ ስለምንገጥም ከምድቡ እናልፋለን፡፡ ይህ አዎንታዊ ጎኑ ነው፡፡”

ተስፋ

“አብዛኞቹ ተጫዋቾች ለአፍሪካ ዋንጫ አዲስ ናቸው፡፡ ግን ይህ ቡድን በአውሮፓ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ከቀደምት ግዜያት በላይ ይዟል፡፡ ሳላህ፣ ኤልኒኒ፣ ፣ ኮካ፣ ኤልማሃመዲ፣ ኦማር ጋብር እና ረመዳን ሶብሂን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ልምድ ካላቻው ተጨዋቾች በተጓዳኝ የሶሰት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኖቹን ቡድን ውስጥ የተጫወቱት ኤልሃድሪ እና አህመድ ፋቲ አሉ፡፡ ከምድብ ካለፍን በእርግጠኛነት ግማሽ ፍፃሜ እንደርሳለን፡፡ ከእዛ በኃላ ማንኛውም ነገር ሊፈጠር ይችላል፡፡”

የመሃመድ ሳላህ ጥገኛ መሆን

“አሁን ላይ እጅግ በጣም አጥብቆ የመከላከል አጨዋወት ነው የምንጫወተው፡፡ በሺአታ ግዜ እንደነበረው የተመጣጠነ እና ማራኪ እግርኳስን አንጫወትም፡፡ ይህ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ላይ ጥገኛ እንድንሆን አድርጎናል፡፡ ሳላህ ደግሞ ይህንን አጨዋወት ለመከወን የተካነ ነው፡፡ ብዙ ጥሩ ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ አሉ ነገር ግን ሳላህ በጣም ውጤታማ ነው፡፡”

ስጋት

“አጥቂዎቻችን መጥፎ የሚባሉ አይደሉም ግን በመስመር ተጫዋቾቻችን ላይ ጥገኛ ነን፡፡ ከመስመር እየተነሱ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው በቡድኑ ላይ የውጤት ለውጥ የሚያመጣው፡፡ በፊት መስመር ተሰላፊ ግብ ካስቆጠርን አንድ ዓመት አለፈን እሱም ባሰም ሞርሲ ነው ያስቆጠረው፡፡ ከእዛ በኃላ 11 ጨዋታዎችን አድርገን 13 ግቦች አስቆጥረናል፡፡ ግቦቹንም ያስቆጠሩት በአብዛኛው የአማካይ ስፋራ ተጫዋቾች ናቸው፡፡”

ግብፅ በፊት መስመር ተሰላፊዎቿ መሳሳት እጅጉን ብትቸገርም ፈጣን የሆኑት የቡድኑ አማካዮች ግቦችን ለማስቆጠር ሲቸገሩ አይስተዋልም፡፡ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል እና ውጤታማ የሆኑ ግብ ጠባቂዎችን መያዟ ተጋጣሚ ሃገራት እንዲቸገሩ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ቡድኑ የአውሮፓ እግርኳስን የለመዱ ተጨዋቾችን ማካተቱ ይበልጥ በውጤታማነቱ ላይ ተስፋ እንዲሰንቅ ያስችለዋል፡፡

የሚጠበቁ ተጫዋቾች

መሃመድ ሳላህ የቡድኑ ቁልፍ እና እጅግ ወሳኝ ተጫዋች ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ፈጣኑ ሳላህ ግብ ለማስቆጠርም ይሁን ለጓደኞቹ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን በመላክ የሚስተካከለው ተጫዋች የለም፡፡ የእሱ መኖር እና አለመኖር የግብፅ ቡድን ቅርፅ ላይ ያለው ተፅዕኖም እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

ከሳላህ ውጪ የአል አሃሊው ኮከብ አብደላ ኤል-ሳዒድ የሚጠቀስ ተጫዋች ነው፡፡ ኤል-ሳዒድ ታታሪ ከመሆኑ ባሻገር የሜዳውን ሰፊ ስፍራ አካሎ የመጫወት አቅሙ ፈርኦኖቹን የሚጠቅም ይሆናል፡፡ መሃመድ ቴሬዝጌ እና ረመዳን ሶብሂም በመስመር ላይ ያላቸው ፈጣን የሆነ እንቅስቃሴ የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮች የሚረብሽ ነው፡፡ መሃመድ ኤልኒኒ ለተከላካዮች የሚገባውን ሽፋን የሚሰጥ ሲሆን የ43 ዓመቱ ግብ ጠባቂ ኤሳም ኤል-ሃድሪ እና ሻሪፍ ኤክራሚ የፈርኦኖቹን ግብ በመጠበቅ ጥሩ ይሰራሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡

የማጣሪያ ጉዞ

ግብፅ ከናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ እና ቻድ ጋር በምድብ ስድስት ተደልድላ ነበር፡፡ ቻድ ከማጣሪያው በፋይናንስ እጥረት ምክንያት እራሷን ስታገል ለቀሪዎቹ ሶስት ሃገራተ ምድቡ ይበልጥ አስቸጋሪ መልክን ይዟል፡፡ ግብፅ ካደረገቻቸው አራት ጨዋታዎች ሶስት ስታሸንፍ በአንዱ ደግሞ ከሜዳዋ ውጪ ከናይጄሪያ ጋር አቻ ወጥታለች፡፡ በ10 ነጥብ የምድቡ መሪ በመሆን ወደ ጋቦን የሚወስዳትን ትኬት የቆረጠችው፡፡

ሙሉ ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

ኤሳም ኤል-ሃድሪ (ዋዲ ደግላ/ግብፅ)፣ ሻሪክ ኤክራሚ (አል አሃሊ/ግብፅ)፣ አህመድ ኤል-ሸናዊ (ዛማሌክ/ግብፅ)

ተከላካዮች

አሊ ጋብር (ዛማሌክ/ግብፅ)፣ አህመድ ኤል-ሞሃመዲ (ሃል ሲቲ/እንግሊዝ)፣ አህመድ ሄጋዚ (አል አሃሊ/ግብፅ)፣ አህመድ ፋቲ (አል አሃሊ/ግብፅ)፣ አህመድ ዳውዳር (ዛማሌክ/ግብፅ)፣ መሃመድ አብድልሻፊ ካራባ (አል አሃሊ ጅዳ/ ሳውዲ አረቢያ)፣ ካሪም ሃፊዝ (ሬሲንግ ክለብ ደ ሌንስ/ፈረንሳይ)፣ ሳላዲን ሰአድ (አል አሃሊ/ግብፅ) 

አማካዮች

ኦማር ጋብር (ቤዝል/ ስዊዘርላንድ)፣ ኢብራሂም ሳላህ (ዛማሌክ/ግብፅ)፣ ታሪቅ ሃምድ (ዛማሌክ/ግብፅ)፣ መሃሙድ ቴሬዝጌ (ሮያል ሞስክሮን/ቤልጂየም)፣ ረመዳን ሶብሂ (ስቶክ ሲቲ/እንግሊዝ)፣ መሃመድ ኤልኒኒ (አርሰናል/እንግሊዝ)፣ አብደላ ኤል-ሳዒድ (አል አሃሊ/ግብፅ)፣ መሃሙድ ካራባ (ኢቲሃድ ጅዳ/ሳዊዲ አረቢያ)፣ አምር ዋርዳ (ፓናቶሊኮስ አግሪኒዮ/ግሪክ)

አጥቂዎች

አህመድ ሃሰን ኮካ (ስፖርቲግ ብራጋ/ፖርቹጋል)፣ መሃመድ ሳላሃ (ኤኤስ ሮማ/ጣሊያን)፣ ማርዋን ሞሂሰን (አል አሃሊ/ግብፅ)

ግብፅ የምድብ መክፈቻ ጨዋታዋን ማክሰኞ ማሊን በመግጠም ትጀምራለች፡፡

Leave a Reply